የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐጌ 2:1-9

ሐጌ 2:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለይሁዳ አለቃ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁም ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ ስትል ተናገር፦ በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን? አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፥ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱና ሥሩ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፣ አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፣ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ሐጌ 2:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሰባተኛው ወር፣ በሃያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ “ለይሁዳ ገዥ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፣ ለሊቀ ካህናቱ ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፣ ከምርኮ ለተረፈውም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ጠይቃቸው፤ ‘ይህን ቤት በቀድሞ ክብሩ ሳለ ያየ ከመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ ምን መስሎ ይታያችኋል? ይህ በፊታችሁ ምንም እንዳይደለ የሚቈጠር አይደለምን?’ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤ ‘ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ይህ ነው፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይሆናልና አትፍሩ።’ “ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርብ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አንድ ጊዜ አናውጣለሁ። ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር። ‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘የዚህ የአሁኑ ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር ይበልጣል’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘በዚህም ቦታ ሰላምን እሰጣለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት።”

ሐጌ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለይሁዳ አለቃ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁም ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ ስትል ተናገር፦ በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን? አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፥ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱና ሥሩ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፥ አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፥ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ሐጌ 2:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ሰባተኛው ወር በገባ በሃያ አንደኛው ቀን በነቢዩ ሐጌ አማካይነት እግዚአብሔር ዳግመኛ ተናገረ፤ ጌታ ይሁዳ ገዢ ለሆነው ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ሊቀ ካህናት ለሆነው ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱና ተርፎ ከስደት ለተመለሰው ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር አለው። “የዚህ ቤተ መቅደስ የቀድሞ ክብሩ እንዴት እንደ ነበረ ያየ ሰው በእናንተ መካከል አለን? ዛሬስ እንዴት ሆኖ ታዩታላችሁ? ይህ በእናንተ ዘንድ እንደሌለ የሚቈጠር አይደለምን? አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ! በርታ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ! በርታ፤ የሀገሪቱ ሕዝብ ሆይ! በርቱ! እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ። እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ‘እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ’ ብዬ በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት አሁንም መንፈሴ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ አይዞአችሁ አትፍሩ” ብሎ ነገራቸው። የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ መንግሥታትን ሁሉ እገለብጣለሁ፤ ሀብታቸውንም ሁሉ ወደዚህ እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሀብት የተሞላ ይሆናል። በዓለም የሚገኝ ወርቅና ብር ሁሉ የእኔ ነው። አዲሱ ቤተ መቅደስ ከፊተኛው ይበልጥ የተዋበ ይሆናል፤ እኔም በዚያ ለሕዝቤ የተሟላ ሰላምን እሰጣለሁ፤” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።

ሐጌ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ለይሁዳ ገዢ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁ ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምንም አይደለምን? አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል ጌታ፤ ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፤ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱ፥ ይላል ጌታ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ነው መንፈሴ በመካከላችሁ ይቆማልና አትፍሩ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እንደገና በቅርብ ጊዜ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ መንግሥታትን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በመንግሥታት ሁሉ ውድ የሆነ ዕቃም ይመጣል፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።