ዘፍጥረት 50:1-26
ዘፍጥረት 50:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዮሴፍ በአባቱ ሬሳ ላይ ወደቀና ፊቱን እየሳመ አለቀሰ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። መድኃኒት ቀማሚዎቹም በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው። ግብጻውያን ሰባ ቀን ሙሉ አለቀሱለት። የለቅሶው ወራት በተፈጸመ ጊዜ ዮሴፍ የፈርዖንን ባለ ሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፦ “መልካም ፈቃዳችሁ ቢሆን እባካችሁ ለፈርዖን፥ ‘አባቴ ለመሞት ሲቃረብ በከነዓን ምድር ባዘጋጀው መቃብር እንድቀብረው በመሐላ ቃል አስገብቶኛል፤ ስለዚህ እዚያ ሄጄ አባቴን ቀብሬ እንድመለስ ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቆአል’ ብላችሁ ንገሩልኝ” አላቸው። ፈርዖንም ይህን ሰምቶ “ቃል በገባህለት መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው። ስለዚህ ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ሄደ፤ የፈርዖን ባለሥልጣኖችና በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ ታላላቅ ሰዎች፥ ሌሎችም የግብጽ መኳንንት ዮሴፍን ተከትለው ሄዱ። እንዲሁም የዮሴፍ ቤተሰቦች፥ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተሰቦች ሁሉ ከዮሴፍ ጋር ሄዱ፤ በጌሴም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፥ በጎቻቸው፥ ፍየሎቻቸውና ከብቶቻቸው ብቻ ነበሩ። ባለ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከትለውት ወጡ፤ በጠቅላላው የተከተለው አጀብ እጅግ ብዙ ነበር። ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ “አጣድ” ተብላ ወደምትጠራው አውድማ ደረሱ፤ እዚያም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ አለቀሱ፤ ዮሴፍም እዚያ ሰባት ቀን ሙሉ የሐዘን ውሎ አደረገ። በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ አውድማ ለቅሶውን ባዩ ጊዜ “ይህ የግብጻውያን ለቅሶ እንዴት መሪር ነው?” አሉ። በዚህ ምክንያት በዮርዳኖስ ሜዳ ያለው የዚያ ቦታ ስም “አቤል ምጽራይም” ተባለ፤ ትርጒሙም በዕብራይስጥ “የግብጻውያን ለቅሶ” ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ የያዕቆብ ልጆች አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አስከሬኑን ወደ ከነዓን ወስደው ከመምሬ በስተምሥራቅ በምትገኘው በማክፌላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ አብርሃም ለመቃብር ቦታ እንዲሆን ከሒታዊው ከዔፍሮን በገዛው እርሻ ውስጥ የሚገኝ ነው። ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ ከወንድሞቹና ለቀብር አጅበውት ከሄዱት ሰዎች ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ግብጽ ተመለሰ። የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው ከሞተ በኋላ “ዮሴፍ ባደረስንበት በደል ሁሉ እስከ አሁንም ቂም ይዞ ሊበቀለን ቢፈልግ ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት፥ ‘ወንድሞችህ በበደሉህ ጊዜ ያደረሱብህን ጒዳት ሁሉ አትቊጠርባቸው ብሎሃል’ ብለን እንድንነግርህ አዞናል፤ ስለዚህ እኛ የአባትህ አምላክ አገልጋዮች ያደረስንብህን በደል ሁሉ ይቅር እንድትለን እንለምንሃለን።” ዮሴፍ ይህን በሰማ ጊዜ አለቀሰ። ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ራሳቸው በፊቱ ቀርበው ጐንበስ ብለው እጅ ነሡና “እነሆ እኛ ሁላችን አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ነገር ግን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን አይደለሁም፤ በእርግጥ እናንተ ክፉ ነገር መክራችሁብኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ወደ መልካም ነገር ለወጠው፤ ይህንንም ያደረገው አሁን በሕይወት ያሉትን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ ነው። ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” በዚህም ዐይነት በመልካም ንግግር በማጽናናት አረጋጋቸው። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ከዚያም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት እስኪሆነው ኖረ፤ የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እናንተን ግን እግዚአብሔር በረድኤት ይጐበኛችኋል፤ ከዚህም አገር አውጥቶ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በመሐላ ቃል ወደ ገባላቸው ምድር ይመልሳችኋል። እግዚአብሔር በሚጐበኛችሁና ወደዚያች ምድር በሚመልሳችሁ ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ ይዛችሁ የምትወጡ መሆናችሁን በማረጋገጥ ቃል ግቡልኝ” ብሎ አስማላቸው። ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ አስከሬኑንም በሽቶ አሽተው በማድረቅ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፤ በእርሱም ላይ አለቀሰ፤ ሳመውም። ዮሴፍም ባለ መድኀኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለ መድኀኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት። አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ ሽቱ የሚቀቡበትን ቀን እንዲሁ ይቈጥራሉና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት። የልቅሶውም ወራት ከተፈጸመ በኋላ ዮሴፍ ለፈርዖን መኳንንት እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ “እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ስለ እኔ ንገሩት፦ አባቴ ሳይሞት አምሎኛል፤ እንዲህ ሲል፦ ‘እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር በዚያ ቅበረኝ።’ አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።” ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ውጣ፤ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው።” ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎሌዎችም ሁሉ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም ሁሉ፥ የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፤ የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ፥ ወንድሞቹም፥ የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም ብቻ በጌሤም ተዉ። ሰረገሎችም፥ ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፤ ሠራዊቱም ብዙ ነበር። በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ ደረሱ፤ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ በአዩ ጊዜ፥ “የግብፅ ልቅሶ እንዲህ ታላቅ ነውን?” አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም “ላሐ ግብፅ” ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር መለሱት፤ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። ዮሴፍና ወንድሞቹ፥ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ። የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ በአዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፥ “ምናልባት ዮሴፍ ያደረግንበትን ክፋት ያስብብን ይሆናል፤ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” ወደ ዮሴፍም መጡ፤ እንዲህም አሉት፥ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዟል፦ ‘ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህ የወንድሞችህን በደል ኀጢአታቸውንም ይቅር በል፤ እነርሱ በአንተ ክፉ አድርገውብሃልና፤’ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።” ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ፤ “እነሆ፥ እኛ ለአንተ አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ዮሴፍም አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖአልና። እናንተ በእኔ ላይ ክፉ መከራችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲመገብ ለማድረግ ለእኔ መልካም መከረ። አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ቤተ ሰቦቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም፤ በልባቸው የሚገባ ነገርም ነገራቸው። ዮሴፍም በግብፅ ሀገር ተቀመጠ፤ እርሱና ወንድሞቹ የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ። የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ዮሴፍም ወንድሞቹን አላቸው፥ “እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጐብኘትን ይጐበኛችኋል፤ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያገባችኋል።” ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፥ “እግዚአብሔር በጐበኛችሁ ጊዜ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር አውጡ” ብሎ አማላቸው። ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፤ በግብፅ ምድርም በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዮሴፍ በአባቱ ፊት ተደፍቶ አለቀሰ፤ ሳመውም። ከዚያም ዮሴፍ የአባቱ የእስራኤል ሬሳ እንዳይፈርስ ባለመድኀኒት የሆኑ አገልጋዮቹ በመድኀኒት እንዲቀቡት አዘዘ። ባለመድኀኒቶቹም እንዳይፈርስ ሬሳውን በመድኀኒት ቀቡት። ሬሳው እንዳይፈርስ መድኀኒት መቀባቱ በአገሩ ልማድ መሠረት አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ግብጻውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት። የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩልኝ፤ ‘የምሞትበት ጊዜ ስለ ተቃረበ፣ በከነዓን ምድር ራሴ ቈፍሬ በአዘጋጀሁት መቃብር እንድትቀብረኝ’ ሲል አባቴ አስምሎኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ልቅበር፤ ከዚያም እመለሳለሁ።” ፈርዖንም፣ “በአስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው። ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንዲሁም የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት። እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ ዐብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ። እንዲሁም ሠረገሎችና ፈረሰኞች ዐብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበረ። እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ልቅሶ ተቀመጠ። በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብጻውያን መራራ ልቅሷቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር። የያዕቆብ ልጆችም አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አስከሬኑን ወደ ከነዓን ምድር ወስደው አብርሃም ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ላይ ከነዕርሻው በገዛው፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት። ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ፣ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር ዐብረውት ሄደው ከነበሩት ሁሉ ጋራ ወደ ግብጽ ተመለሰ። የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም የእኛን የአባትህን አምላክ አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት። ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር ቦታ ማን አስቀመጠኝ? እናንተ እኔን ለመጕዳት ዐስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦ፣ በደግ ቃል አናገራቸው። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋራ በግብጽ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤ የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ። የምናሴ ልጅ ማኪር የወለዳቸውም ልጆች በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን፣ “እነሆ፤ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቧል፤ እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይጐበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፣ “እግዚአብሔር በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያ ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” ሲል አስማላቸው። ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ፤ ሬሳው እንዳይፈርስ በአገሩ ደንብ በመድኀኒት ከደረቀ በኋላ፣ ሣጥን ውስጥ አስገብተው በግብጽ ምድር አስቀመጡት።
ዘፍጥረት 50:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮች አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት። አርባ ቀንም ፈጸሙለት የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልን የግብፅም ሰዎች ሰባ ቅን አለቀሱለት። የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዓን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ አባቴ አምሎኛልን እንዲ ሲል፦ እነሆ እኔ እሞታለሁ በቋፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ። ፈርዖንም፦ ውጣ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው። ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤ የዮሴፍም ቤተ ስቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተሰቦች ወጡ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተው። ሰረጎሎችም ፈረሶኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ ሠራዎቱም እጅግ ብዙ ነበረ። በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ስዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፦ ይህ ለግብፅ ሰዎች ታልቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት እርሱም በዮርዳኖች ማዶ ነው። ልጆቹም እንድዘዛቸው እንድዚያው አደረጉለት፤ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጡያዊ ከኤፍሮን ከእርሽ ጋር የገዛት ዋሻ ናት ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበር በኍላ ወደ ግብፅ ተመለሱ። የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዪ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ ምናልባትም ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል ባደረግንበትን ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል። ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህ የውንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና አሁን እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉን ይቅር በል። ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ዮሴፍም አላቸው፦ አትፍሩ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን? እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ እኔ እናንተና ልጆቻችሁን እመግባችኍለሁ አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ እርሱና የአባቱም ቤተ ስብ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ። ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ፦ እኔ እሞታለሁ እግዚአብሔር መጎብኘትን ይጎበኛችኍል ከዚህችም ምድር ያወጣችኍል ለአብርሃምን ለይስሕቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኍል። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚን አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው። ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ በሽቱ፥ አሹት በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም። ዮሴፍም አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። መድኃኒት ቀማሚዎቹም በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው። ግብጻውያን ሰባ ቀን ሙሉ አለቀሱለት። የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደሆን ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ አባቴ፦ ‘እነሆ እኔ እሞታለሁ፥ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ’ ሲል አስምሎኛል። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።” ፈርዖንም፦ “ሂድ፥ አባትህን እንዳስማለህ ቅበረው” አለው። ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፥ የፈርዖን አገልጋዮቹም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችና የግብጽ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፥ የዮሴፍም ቤተሰቦች ሁሉ፥ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተሰቦች ወጡ፥ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ። ሰረጎሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ። በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፥ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፦ “ይህ ለግብጽ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፥” ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፥ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፥ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፥ እርሷም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብጽ ተመለሱ። የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ “ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ ‘እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፥ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባርያዎች የበደሉህን ይቅር በል።’” ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ “እነሆ እኛ ለአንተ ባርያዎችህ ነን አሉት።” ዮሴፍም አላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን ነኝ? እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ፥ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ፥ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ “እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ “እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ” አስማላቸው። ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ በሽቶም አሹት፥ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።