ዘፍጥረት 45:4-15

ዘፍጥረት 45:4-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዮሴ​ፍም ወን​ድ​ሞ​ቹን፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላ​ቸው። ወደ እር​ሱም ቀረቡ። እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ወደ ግብፅ የሸ​ጣ​ች​ሁኝ እኔ ወን​ድ​ማ​ችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁ​ንም ወደ​ዚህ ስለ​ሸ​ጣ​ች​ሁኝ አት​ፍሩ፤ አት​ቈ​ር​ቈ​ሩም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሕ​ይ​ወት ከእ​ና​ንተ በፊት ልኮ​ኛ​ልና። እነሆ፥ ይህ ሁለቱ ዓመት በም​ድር ላይ ራብ የሆ​ነ​በት ነውና፤ የማ​ይ​ታ​ረ​ስ​በ​ትና የማ​ይ​ታ​ጨ​ድ​በት አም​ስት ዓመት ገና አለ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በም​ድር ላይ እን​ድ​ት​ድ​ኑና እን​ድ​ት​ተ​ርፉ እመ​ግ​ባ​ችሁ ዘንድ ከእ​ና​ንተ በፊት ላከኝ። አሁ​ንም እና​ንተ ወደ​ዚህ የላ​ካ​ች​ሁኝ አይ​ደ​ላ​ች​ሁም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈ​ር​ዖ​ንም እንደ አባት አደ​ረ​ገኝ፤ በቤ​ቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግ​ብፅ ምድ​ርም ሁሉ ላይ አለቃ አደ​ረ​ገኝ። አሁ​ንም ፈጥ​ና​ችሁ ወደ አባቴ ሂዱ፤ እን​ዲ​ህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚ​ለው ነገር ይህ ነው፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በግ​ብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደ​ረ​ገኝ፤ ወደ እኔ ና፤ በዚ​ያም አት​ዘ​ግይ፤ በዐ​ረብ በኩል በጌ​ሤም ምድ​ርም ትቀ​መ​ጣ​ለህ፤ ወደ እኔም ትቀ​ር​ባ​ለህ። አን​ተና ልጆ​ችህ የል​ጆ​ች​ህም ልጆች፥ በጎ​ች​ህና ላሞ​ችህ፥ የአ​ንተ የሆ​ነው ሁሉ፥ በዚ​ያም አን​ተና የቤ​ትህ ሰዎች የአ​ንተ የሆ​ነው ሁሉ እን​ዳ​ት​ቸ​ገሩ እመ​ግ​ብ​ሃ​ለሁ፤ የራቡ ዘመን ገና አም​ስት ዓመት ቀር​ቶ​አ​ልና፤ እነ​ሆም፥ ለእ​ና​ንተ እኔ ራሴ በአፌ እንደ ተና​ገ​ር​ሁ​አ​ችሁ እና​ንተ በዐ​ይ​ኖ​ቻ​ችሁ አይ​ታ​ች​ኋል፤ ወን​ድሜ ብን​ያም በዐ​ዓ​ይ​ኖቹ አይ​ቶ​አል። ለአ​ባቴ በግ​ብፅ ምድር ያለ​ኝን ክብ​ሬን ሁሉ፥ በዐ​ይ​ኖ​ቻ​ችሁ ያያ​ች​ሁ​ት​ንም ሁሉ ንገ​ሩት፤ አባ​ቴ​ንም ወደ​ዚህ ፈጥ​ና​ችሁ አም​ጡት።” የወ​ን​ድ​ሙን የብ​ን​ያ​ም​ንም አን​ገት አቅፎ አለ​ቀሰ፤ ብን​ያ​ምም በአ​ን​ገቱ ላይ አለ​ቀሰ። ወን​ድ​ሞ​ቹን ሁሉ ሳማ​ቸው፤ በእ​ነ​ር​ሱም ላይ አለ​ቀሰ፤ ከዚ​ያም በኋላ ወን​ድ​ሞቹ ከእ​ርሱ ጋር ተጨ​ዋ​ወቱ።

ዘፍጥረት 45:4-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስኪ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፤ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አሁንም በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው ዐምስት ዓመታት ገና አሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። “ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብጽ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ። አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። ገና ወደ ፊት የሚመጣ የዐምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ አለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’ “ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው። በግብጽ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።” ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው። የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከርሱ ጋራ መጨዋወት ጀመሩ።

ዘፍጥረት 45:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ አትቆርቆሩም እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና። ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ ወደ እኔም ትቀርባለህ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፤ በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና። እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት። የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው በእነርሱም ላይ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።

ዘፍጥረት 45:4-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚህ ጊዜ ዮሴፍ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፦ ከቀረቡም በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ ነገር ግን ይህን በማድረጋችሁ በመጸጸት አትበሳጩ፤ እግዚአብሔር እኔን አስቀድሞ የላከኝ የሰዎችን ሕይወት እንዳተርፍ ነው። በምድር ላይ ራብ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዞአል፤ ሰዎች አርሰው መከር መሰብሰብ የማይችሉባቸው አምስት ዓመቶች ገና ይመጣሉ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ወደዚህ የላከኝ በዚህ በአስደናቂ ዘዴ የእናንተን ሕይወት በማዳን በምድር ላይ ዘር እንዲቀርላችሁ አስቦ ነው። “ስለዚህ ወደዚህ የላከኝ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ለፈርዖን እንደ መካሪ አባት፥ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታና የመላው ግብጽ አገር ገዢ አደረገኝ። አሁን በፍጥነት ተመልሳችሁ ወደ አባቴ ሂዱና ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይልሃል በሉት፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ገዢ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና፤ ልጆችህን፥ የልጅ ልጆችህን፥ በጎችህን፥ ፍየሎችህን፥ ከብቶችህን ሌላም ያለህን ነገር ሁሉ ይዘህ ና፥ በእኔው አቅራቢያ በሚገኘው በጌሴም ምድር ትኖራለህ። አምስት የራብ ዓመቶች ገና ስለሚቀሩ አንተና ቤተሰብህ እንስሶችህም ጭምር ራብ እንዳይደርስባችሁ በጌሴም እመግብሃለሁ።’ ” ቀጥሎም ዮሴፍ እንዲህ አለ፤ “አሁን የምናገራችሁ እኔ ዮሴፍ መሆኔን እናንተና አንተም ወንድሜ ብንያም አይታችሁ ለማረጋገጥ ችላችኋል፤ በግብጽ አገር ያለኝን ታላቅ ክብርና ያያችሁትንም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ በፍጥነትም ወደዚህ አምጡት።” ከዚህ በኋላ የወንድሙን የብንያምን አንገት ዐቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም ወንድሙን ዐቅፎ አለቀሰ፤ ዮሴፍ የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ ባንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መነጋገር ጀመሩ።

ዘፍጥረት 45:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዮሴፍም ወንድሞቹን “እስቲ ወደ እኔ ቅረቡ” አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፥ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። ይህ በምድር ላይ ሁለት ዓመት ራብ የሆነበት ነው፥ ገና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ይመጣል። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፥ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብጽ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፥ ከእኔም በቅርበት፥ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ። በዚያም፥ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፥ አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ።’ እነሆም የተናገረቻችሁ የእኔ አንደበት እንደ ሆነች የእናንተ ዐይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዐይኖች አይተዋል። ለአባቴም በግብጽ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፥ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፥ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፥ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።