ዘፍጥረት 41:1-40
ዘፍጥረት 41:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሁለት ዓመት በኋላም ፈርዖን ሕልምን አየ፤ እነሆም፥ በወንዙ ዳር ቆሞ ነበር። እነሆም፥ መልካቸው ያማረ፥ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ በወንዙም ዳር በመስኩ ይሰማሩ ነበር። ከእነርሱም በኋላ እነሆ፥ መልካቸው የከፋ፥ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ተሰማርተው ነበር። መልካቸው የከፋ፥ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያ ሰባት ላሞች መልካቸው ያማረውን፥ ሥጋቸውም የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ፤ ደግሞም ተኛ፤ ሁለተኛ ሕልምንም አየ፤ እነሆም፥ በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ፥ ያማሩና ምርጥ የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ እነሆም፥ ከእነርሱ በኋላ የሰለቱና በነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ እነዚያም የሰለቱና ነፋስ የመታቸው እሸቶች ሰባቱን ያማሩና የጐመሩ እሸቶች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ፤ እነሆም ሕልም ነበር። በነጋም ጊዜ መንፈሱ ታወከችበት፤ የግብፅ ሕልም ተርጓሚዎችንና ጠቢባንን ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው፤ ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን ሕልሙን የሚተረጕምለት አልተገኘም። የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ፥ “እኔ ኀጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤ ፈርዖን በአገልጋዮቹ ላይ ተቈጣ፤ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ቤት አኖረን፤ እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን፤ እኔና እርሱ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን። በዚያም የእንጀራ አበዛዎች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጐልማሳ ከእኛ ጋር ነበር፤ ለእርሱም ነገርነው፤ ሕልማችንንም ተረጐመልን። እንዲህም ሆነ፤ እንደ ተረጐመልን እንደዚያው ሆነ፤ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ፤ እርሱም ተሰቀለ።” ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራው፤ ከግዞት ቤትም አወጡት፤ ራሱንም ላጩት፤ ልብሱንም ለወጡ፤ ወደ ፈርዖንም ገባ። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ሕልምን አየሁ፤ የሚተረጕምልኝም አጣሁ፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ።” ዮሴፍም፥ “እግዚአብሔር ከገለጸለት ሰው በቀር መተርጐም የሚችል የለም” ብሎ ለፈርዖን መለሰለት። ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ፥ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፤ በወንዙ ዳር በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ፥ የደከሙ፥ መልካቸውም እጅግ የከፋ፥ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤ እነዚያ የከሱትና መልከ ክፉዎቹ ላሞች እነዚያን የመጀመሪያዎቹን ያማሩና የወፈሩ ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፤ በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም ውስጥ የገባ እንደሌለ ሆኑ፤ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ፤ ነቃሁም። ዳግመኛም ተኛሁ፤ በሕልሜም እነሆ፥ የጐመሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ከአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ የሰለቱና በነፋስ የተመቱ ሌሎች ሰባት እሸቶች ወጡ፤ እነዚያ የሰለቱትና በነፋስ የተመቱት እሸቶች እነዚያን ያማሩትንና የጐመሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ፤ የተረጐመልኝም የለም።” ዮሴፍም ፈርዖንን አለው፥ “የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳይቶታል። እነዚያ ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እነዚያም ሰባቱ መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው። ከእነርሱም በኋላ የወጡት እነዚያ የከሱና መልከ ክፉዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እነዚያም የሰለቱትና ነፋስ የመታቸው ሰባቱ እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው። ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው። እነሆ፥ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤ ደግሞም ከዚህ በኋላ ሰባት የራብ ዓመት ይመጣል፤ በግብፅ ሀገር ሁሉ የነበረውንም ጥጋብ ሁሉ ይረሱታል፤ ራብም ምድርን ሁሉ ያጠፋል፤ በኋላም ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣ በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፤ እጅግ ጽኑ ይሆናልና። ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል። አሁንም ብልህና ዐዋቂ ሰውን ለአንተ ፈልግ፤ በግብፅ ምድር ላይም ሹመው። ፈርዖን በግብፅ ምድር ላይ ሹሞችን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ። የሚመጡትን የመልካሞቹን ሰባት ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፤ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ። በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ለሀገሩ ሁሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም።” ነገሩም ፈርዖንንና ሰዎቹን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው፥ “በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰውን እናገኛለን?” ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና ከአንተ ይልቅ ብልህና ዐዋቂ ሰው የለም። አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፤ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔም ከዙፋኔ በቀር ከአንተ የምበልጥበት የለም።”
ዘፍጥረት 41:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ እነሆ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጧቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፤ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጕምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጕም ነበረው። በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።” ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጕሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ። ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጕምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለፈርዖን የሚሻውን ትርጕም ይሰጠዋል” አለው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። ከእነርሱም በኋላ፣ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። “እንደዚሁም፣ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።” ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። “አስቀድሜ ለፈርዖን እንደ ተናገርሁት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። “እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። ሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።” ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንደ አንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”
ዘፍጥረት 41:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሁለት ዓመት በኍላም ፈርዖን ሕልምን አየ፥ እነሆም በወንዙ ዳር ቆሞ ነበረ። እነሆም መልካቸው ያማረ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ በውኃውም ዳር በመስኩ ይስማሩ ነበር። ከእነርሱም በኍላ እነሆ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዝ ወጡ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ይቆሙ ነበር። መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያም ላሞች መልካቸው ያማረውን ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ። ደግሞም ተኛ ሁለተኛም ሕልምን አየ እነሆም በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ ያማሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ። እነሆም ከእነርሱ በኍላ የሰለቱና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ የሰለቱትም እሽቶች ስባቱን ያማሩና የዳበሩ እሸቶች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ እነሆም ሕልም ነበረ። በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታወከችበት ወደ ሕልም ተርጕሚዎች ሁሉ ወድ ግብፅ ጠቢባንም ሁሉ ልኮ ወደ እርሱ ጠራቸው ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን የሚተረጕም አልተገኘም። የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፈዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ፦ እኔ ኃጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤ ፈርዖን በባሪይዎቹ ላይ ተቆጣ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ስፍራ በዘበኞች አለቃ ቤት አኖረን እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን እኔና እርሱ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን። በዚይም የዘበኞቹ አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጕልማሳ ከእኛ ጋር ነበረ ለእርሱም ነገር ነው ሕልማችንንም፥ ተረጎመልን። እንዲህም ሆነ እንደ ተረጎመልን እንደዚያው ሆነ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ እርሱም ተሰቀለ። ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራ ከግዞት ቤትም አስቸኮሉት፤ እርሱም ተላጨ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ ፈርዖን ገባ። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ ሕልምን አየሁ የሚተረጕመውም አልተገኘም ሕልምን እንደ ሰማህ እንደ ተረጎምህም ስለ አንተ ሰማሁ። ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ይህ በእኔ አይደለም እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በደኅንነት ይመልስለታል። ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው፦ እነሆ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ እነሆም ሥጋቸውም የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ በመስኩም ይስማሩ ነበር። ከእነርሱን በኍላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልክ ከፍ ከቶ አላየሁም፤ የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ወፍራሞቹን ስባት ላሞች ዋጡአቸው፥ በሆዳቸውም ተዋጡ አልታወቀም መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረውም የከፋ ነበረ። በሕልሜም እነሆ የዳበሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች በአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ ከእነርሱም በኍላ እነሆ የደረቁና የሰለቱ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ስባት እሸቶች ወጡ የሰለቱት እሸቶች ያማሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ የሚተረጕምልኝም አጣሁ። ዮሴፍም ፈርዖንን አለው፦ የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን ነግሮታል። ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው ሕልሙ አንድ ነው። ከእነርሱም በኍላ የወጡት የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ የሰለቱትና የምሥራቅ ነፋስ የመታቸው ሰባቱም እሽቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው። ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው። እነሆ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ ደግሞ ከዚህ በኍላ የሰባት ዓመት ራብ ይመጣል በግብፅ አገር የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል ራብም ምድርን በጣም ያጠፋል በኍላ ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣም በምድር የሆነው ጥጋብ አያታወቅም እጅግ ጽኑ ይሆናልና። ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀረጠ ስለ ሆነ ነው እግዚአብሔር ፈጥኖ ያደርገዋል። አሁንም ፈርዖም ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው። ፈርዖን በምድር ላይ ሹማምትን ይሹም በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ። የሚመጡትን የመልካሞቹን ዓመታት እህላቸውም ያከማቹ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፥ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ስባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ተጠብቆ ይኑር ምድሪቱም በራብ አትጠፋም። ነገሩም በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆነ፤ ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው፦ በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን? ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና። አንተ በቤቴ ላይ ተሾምክ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ።
ዘፍጥረት 41:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሁለት ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሕልም አየ፤ እርሱ በሕልሙ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ ሰባት የወፈሩና የሰቡ ላሞች ከወንዙ ወጥተው ሣር ሲበሉ አየ፤ ቀጥሎም አጥንታቸው እስከሚታይ የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወንዙ ዳር ከነበሩት ላሞች አጠገብ ቆሙ። የከሱት ላሞች የወፈሩትን ላሞች ዋጡአቸው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከእንቅልፉ ነቃ። ተመልሶም እንቅልፍ በወሰደው ጊዜ እንደገና ሌላ ሕልም አየ፤ በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች አየ፤ ቀጥሎም የቀጨጩና ከበረሓ በተነሣ የምሥራቅ ነፋስ ተመተው የሰለቱ ሰባት የእሸት ዛላዎች በቅለው አየ። ሰባቱም የቀጨጩ የእሸት ዛላዎች፥ ሰባቱን የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጡአቸው፤ ንጉሡም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ሕልም ማየቱን ተገነዘበ። ጠዋት ከመኝታው ሲነሣ መንፈሱ ታወከ፤ ስለዚህ በግብጽ ምድር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች ሁሉ አስጠርቶ ሕልሙን ነገራቸው፤ ነገር ግን የሕልሞቹን ትርጒም ለመግለጥ የቻለ አንድ እንኳ አልነበረም። በዚህ ጊዜ የወይን ጠጅ አሳላፊው ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁትን በደል ዛሬ አስታውሳለሁ፤ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ በእኔና በእንጀራ ቤት ኀላፊው ላይ ተቈጥተህ በዘበኞች አለቃ ቤት እንድንታሰር አድርገህ ነበር፤ በዚያ ሳለን በአንድ ሌሊት ሁለታችንም የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የተለያየ ትርጕም ነበረው። የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የነበረ አንድ ወጣት ዕብራዊ ከእኛ ጋር በእስር ቤት ነበር፤ የእያንዳንዳችንን ሕልም ለእርሱ ነገርነውና ተረጐመልን። ሁሉም ነገር እርሱ እንዳለው ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ማዕርጌ እንድመለስ ተደረገ የእንጀራ ቤቱ ኀላፊ ግን እንዲሰቀል ተደረገ።” ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወዲያውኑ ከእስር ቤት ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩን ተላጭቶ ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ንጉሡ ፊት ቀረበ። ንጉሡም ዮሴፍን “ሕልም አይቼ ነበር፤ ነገር ግን ማንም ሊተረጒመው አልቻለም፤ አንተ ሕልም የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰምቼአለሁ” አለው። ዮሴፍም “ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ሕልም የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ትክክለኛውን ትርጒም ሊሰጥህ የሚችል እግዚአብሔር ነው” አለ። ንጉሡም እንዲህ አለ፤ “በሕልሜ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ ሰባት የወፈሩና የሰቡ ላሞች ከወንዙ ወጥተው ሣር ሲበሉ አየሁ፤ ቀጥሎም አጥንቶቻቸው እስከሚታይ ድረስ የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ እንደ እነርሱ የሚያስከፉ ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። የከሱትና አስከፊ የሆኑት ላሞች በመጀመሪያ የወጡትን ሰባት የወፈሩ ላሞች ዋጡአቸው። ከዋጡአቸውም በኋላ እንደ ቀድሞው የከሱ ስለ ነበሩ፥ እንደ ዋጡአቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ በዚህ ጊዜ እኔ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ደግሞም በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች አየሁ፤ ቀጥሎም የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ ሰባት የእሸት ዛላዎች ታዩ። የቀጨጩትም ዛላዎች የሚያምሩትን ዛላዎች ዋጡአቸው፤ ያየኋቸውንም ሕልሞች ለአስማተኞች ነገርኩ፤ ነገር ግን ሕልሞቹን ማንም ሊተረጒምልኝ አልቻለም።” ዮሴፍም ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሁለቱም ሕልሞችህ ትርጒም አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ ሰባቱ የሚያምሩ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ ሰባቱም ያማሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው። ከእነርሱም በኋላ የወጡት ሰባት የከሱትና አስከፊዎቹ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ እንዲሁም ሰባቱ የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው፤ ይኸውም ሰባት የራብ ዓመቶች ናቸው። ልክ እንደ ነገርኩህ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ በመላው የግብጽ ምድር ላይ ታላቅ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመቶች ይመጣሉ። ከዚያ በኋላ ሰባት የራብ ዓመቶች ይመጣሉ፤ ራብ አገሪቱን በብርቱ ስለሚጐዳት እነዚያ የጥጋብ ዓመቶች ይረሳሉ። ተከታዩ የራብ ዘመን እጅግ አሠቃቂ ስለሚሆን የጥጋብ ጊዜ ፈጽሞ እንዳልነበረ ይሆናል። ሕልሙን ደጋግመህ ማየትህ የሚያመለክተው፥ ነገሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነና በቅርብ ጊዜም ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን ነው። “እንግዲህ ጥበብና ማስተዋል ያለውን ሰው መርጠህ በአገሪቱ አስተዳዳሪ አድርገህ ሹመው፤ በሰባቱ የጥጋብ ዓመቶች አንድ አምስተኛውን ሰብል የሚሰበስቡ ሰዎችን መርጠህ ሹም። እነርሱ በሚመጡት የጥጋብ ዓመቶች ትርፍ የሆነውን ሰብል ሁሉ እንዲሰበስቡ እዘዛቸው፤ በየከተማውም እህል በጐተራ እንዲያከማቹና እንዲጠብቁት ሥልጣን ስጣቸው። ይህም የሚከማቸው እህል በግብጽ ምድር ላይ ወደፊት በሚመጡት ሰባት የራብ ዓመቶች ለአገሪቱ መጠባበቂያ ይሆናል፤ በዚህ ሁኔታ አገሪቱ በራብ ከመጐዳት ትድናለች።” ዕቅዱም ለፈርዖንና ለባለሟሎቹ ሁሉ መልካም ሆኖ ታያቸው፤ ንጉሡም “የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረበት ከዮሴፍ የተሻለ ሰው ከቶ አናገኝም” አላቸው። ስለዚህ ንጉሡ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ይህን ሁሉ የገለጠልህ እግዚአብሔር ነው፤ ከማንኛውም ሰው ይልቅ አስተዋይና ብልኅ መሆንህ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተን በአገሬ ላይ አስተዳዳሪ አድርጌ እሾምሃለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይታዘዝሃል፤ በሥልጣንም ከእኔ በቀር የሚበልጥህ የለም።
ዘፍጥረት 41:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፥ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ እነሆ መልካቸው ያማረ፥ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፥ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፥ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። ፈርዖንም እንደገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፥ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብጽ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፥ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው። በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፥ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።” ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጉሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ። ፈርዖንም ዮሴፍን፥ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጉምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። ዮሴፍም ፈርዖንን፥ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው። ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። ከእነርሱም በኋላ፥ ዐቅመ ደካማ፥ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፥ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። ከዋጧቸውም በኋላ፥ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። እንደዚሁም፥ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።” ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፥ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። በመላው የግብጽ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፥ በግብጽ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፥ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፥ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፥ በመላው የግብጽ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፥ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። የሚከማቸው እህል፥ ወደ ፊት በግብጽ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።” ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። ፈርዖንም፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፥ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”