ዘፍጥረት 4:10-26
ዘፍጥረት 4:10-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም አለው፥ “ቃየል! ምን አደረግህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኀይልዋን አትሰጥህም፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን አለው፥ “ኀጢአቴ ይቅር የማትባል ታላቅ ናትን? እነሆ፥ ዛሬ ከምድር ፊት ከአሳደድኸኝ፥ ከፊትህ እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም አለው፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ ቃየልን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል።” እግዚአብሔርም ቃየልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ቃየልም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ በኤዶም አንጻር ባለችው ኖድ በምትባለው ምድርም ኖረ። ቃየልም ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነስችም፤ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፤ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም “ሄኖሕ” አላት። ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሳኤልን ወለደ፤ ማቱሳኤልም ላሜሕን ወለደ። ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበር። ዓዳም ዮቤልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ኢዮቤል ነበር፤ እርሱም በገናንና መሰንቆን አስተማረ። ሴላም ደግሞ ቶቤልን ወለደች። እርሱም ናስና ብረትን የሚሠራ ሆነ። የእኅቱም ስም ኖሄም ነበረ። ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው፥ “እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፤ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጐልማሳውን ስለ መቍሰሌ፤ ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገድየዋለሁና፤ ቃየልን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።” አዳምም ዳግመኛ ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም ቃየል በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው። ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመረ ነው።
ዘፍጥረት 4:10-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” ቃየንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ። ቃየን ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ሔኖክን ወለደች። ቃየን የቈረቈረውን ከተማ በልጁ ስም ሔኖክ ብሎ ጠራው። ሔኖክ ኢራድን ወለደ፤ ኢራድም መሑያኤልን፣ መሑያኤልም ማቱሣኤልን፣ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ሴላ ነበር። ዓዳ ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ከብት አርቢዎች አባት ነበረ። ወንድሙም ዩባል ይባላል፤ እርሱም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበረ። ሴላም ደግሞ ቱባልቃይን የተባለ ወንድ ልጅ ነበራት፤ እርሱም ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ ነበር። የቱባልቃይን እኅት ናዕማ ትባል ነበር። ላሜሕ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “ዓዳና ሴላ ሆይ ስሙኝ፤ የላሜሕ ሚስቶች ሆይ አድምጡኝ፤ አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣ ጕልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤ ቃየንን የሚገድል ሰባት ጊዜ ቅጣት ካገኘው፣ የላሜሕ ገዳይማ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል።” አዳም እንደ ገና ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ሴት ብላ ጠራችው። ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ።
ዘፍጥረት 4:10-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኽል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፍተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኂይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፤ ኂጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኽኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘንም ሁሉ ይገድለኚል። እግዚአብሔርም እርሱን አለው፤ እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልብታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ፕ ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ። ቃየንም ሚስቱን አወቀ ፀነሰችም፤ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፤ የከተማይቱንም ስም በልጅ ስም ሄኖሕ አላት። ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። ፕ ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፤ የሁለረኚይቱ ስም ሴላ ነበረ። ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ። ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች፤ የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው፤ እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፤ ነገሬን አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቁስሌ፤ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤ ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል። አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፤ ወንድ ልጅንም ወለድች። ስሙንም፤ ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኚል ስትል ሴት አለችው። ለሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደስት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ።
ዘፍጥረት 4:10-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም ቃየልን እንዲህ አለው፤ “ምን አደረግህ? የፈሰሰው የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው፤ የወንድምህን ደም ከአንተ ለመቀበል አፍዋን በከፈተችው ምድር ላይ የተረገምክ ነህ። ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ምንም ፍሬ አትሰጥህም፤ በምድር ላይም ስደተኛ ሆነህ ትንከራተታለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ይህ ቅጣት እኔ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፤ እነሆ፥ ዛሬ ከምድር አባረርከኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ስደተኛና ተንከራታች እሆናለሁ፤ እንግዲህ ማንም ሰው ቢያገኘኝ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን “ማንም አይነካህም፤ አንተን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ቃየልን ማንም ቢያገኘው እንዳይገድለው የሚያስጠነቅቅ ልዩ ምልክት አደረገለት። ከዚህ በኋላ ቃየል ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ ሄደ፤ በዔደን በስተምሥራቅ በሚገኘው በኖድ ምድር ኖረ። ቃየል ሚስቱን ከተገናኘ በኋላ ፀነሰች ሔኖክንም ወለደች፤ ቃየል ከተማን መሠረተ፤ በልጁም ስም “ሔኖክ” ብሎ ጠራት። ሔኖክ ዒራድን ወለደ፤ ዒራድ መሑያኤልን ወለደ፤ መሑያኤል መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤልም ላሜክን ወለደ፤ ላሜክ ዓዳ እና ጺላ የተባሉትን ሁለት ሚስቶች አገባ፤ ዓዳ ያባልን ወለደች፤ ያባልም ከብቶች እየጠበቁ በድንኳን ይኖሩ የነበሩት የዘላኖች ሰዎች አባት ነበረ። የእርሱ ወንድም ዮባልም ዋሽንትና በገና የሚጫወቱ የሙዚቀኞች አባት ነበር። ጺላም “ቱባልቃይን” የተባለ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሱ ከነሐስና ከብረት ልዩ ልዩ ዐይነት ዕቃዎችን ይሠራ ነበር። ቱባልቃይንም ናዕማ የተባለች እኅት ነበረችው። ላሜክ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ እናንተ “ዓዳ እና ጺላ የላሜክ ሚስቶች ሆይ፥ እስቲ አድምጡኝ፥ የምለውን ስሙ፤ አንድ ወጣት መትቶ ስላቈሰለኝ ገደልኩት፤ ቃየልን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል ከተባለ፥ እኔን የሚገድል ደግሞ ሰባ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።” አዳምና ሔዋን ሲገናኙ እንደገና ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እርስዋም “ቃየል በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ወንድ ልጅ ሰጠኝ” ስትል “ሤት” የሚል ስም አወጣችለት። ሤትም “ሄኖስ” የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመሩት በዚያን ጊዜ ነው።
ዘፍጥረት 4:10-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ቃየልን እንዲህ አለው፥ “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየንም ጌታን አለው፦ “ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፥ ከፊትህም እሰወራለሁ፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፥ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም ለእርሱ፥ “እንዲህስ አይሆንም! ማንም ቃየንን የሚገድል፥ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ጌታም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ከዚያም ቃየን ከጌታ ፊት ወጣ፥ ከዔድንም በስተ ምሥራቅ፥ በኖድም ምድር ተቀመጠ። ቃየንም ሚስቱን አወቀ፥ ፀነሰችም፥ ሔኖክንም ወለደች፤ ከተማም መሠረተ፤ ከተማይቱንም በልጁም ስም “ሔኖክ” ብሎ ጠራት። ሔኖክ ዒራድን ወለደ፤ ዒራድ መሑያኤልን ወለደ፤ መሑያኤል መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤልም ላሜሕን ወለደ፤ ላሜሕም ሁለት ሚስቶችን አገባ፥ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ጺላ ነበረ። ዓዳም ያባልን ወለደች፥ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፥ እርሱም በገናንና ዋሽንትን ለሚይዙ አባት ነበረ። ጺላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። ላሜሕም ለሚስቶቹ፥ “ዓዳ እና ጺላ፥ እስቲ አድምጡኝ፥ እናንት የላሜሕ ሚስቶች ሆይ፥ የምለውን ስሙኝ፤ ቢያቆስለኝ ጐልማሳውን ገደልኩ ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገደልኩ፤ “ከሆነ ቃየልን ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት፥ ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።” አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም፥ “ቃየን በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል” ስትል ሤት አለችው። ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም የጌታ ስም በሰው መጠራት ተጀመረ።