ዘፍጥረት 4:1-5
ዘፍጥረት 4:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ቃየልንም ወለደችው። እርስዋም “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደችው። አቤልም በግ ጠባቂ ሆነ፤ ቃየልም ምድርን የሚያርስ ሆነ። ከብዙ ቀን በኋላም እንዲህ ሆነ፤ ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ መጀመሪያ የተወለደውንና ከሰቡት አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየልንም እጅግ አሳዘነው፤ ፊቱም ጠቈረ።
ዘፍጥረት 4:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎቹ መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ።
ዘፍጥረት 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፤ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ። ከብዙ ቀን በኍላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።
ዘፍጥረት 4:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” ስትል “ቃየል” የሚል ስም አወጣችለት። ቀጥሎም የቃየልን ወንድም አቤልን ወለደች፤ አቤል የበጎች ጠባቂ ሆነ፤ ቃየል ግን ገበሬ ሆነ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ካመረተው ሰብል ወስዶ ለእግዚአብሔር መባ አቀረበ። አቤልም ከበጎቹ መንጋ በመጀመሪያ የተወለደውን አንድ ጠቦት አመጣ፤ ካረደውም በኋላ የሰባውንና መልካም የሆነውን ብልት ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እግዚአብሔርም በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ አለው። ለቃየልና ለመሥዋዕቱ ግን ግምት አልሰጣቸውም፤ በዚህ ምክንያት ቃየል በጣም ተቈጣ፤ ፊቱም በቊጣ ተኮሳተረ፤
ዘፍጥረት 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፥ እሷም ፀነሰች፥ ቃየንንም ወለደች። እርሷም፦ “ወንድ ልጅ በጌታ ርዳታ አገኘሁ” አለች። ደግሞም፥ ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፥ ቃየንም መሬትን የሚያርስ ነበረ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለጌታ መሥዋዕትን አቀረበ፥ እንዲሁም አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። ጌታም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፥ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተቈጣ፥ ፊቱም ጠቆረ።