ዘፍጥረት 38:11-19
ዘፍጥረት 38:11-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን፥ “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ” አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞትብኝ ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች። ዘመንዋም በተፈጸመ ጊዜ የይሁዳ ሚስት ሴዋ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፤ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፤ እርሱም ዓዶሎማዊው በግ ጠባቂው ኤራስም። ለምራቱ ትዕማርም፥ “እነሆ፥ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል” ብለው ነገሩአት። እርስዋም የመበለትነቷን ልብስ አወለቀች፤ መጐናጸፊያዋንም ለበሰች፤ ተሸፈነችም፤ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ፥ ሚስትም ትሆነው ዘንድ እርስዋን ሊሰጠው እንዳልፈለገ አይታለችና። ይሁዳም በአያት ጊዜ ዘማ መሰለችው፤ ፊቷን ተሸፍና ነበርና አላወቃትም። ወደ እርስዋም አዘነበለ፥ “እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤” እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም፥ “ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። “የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እልክልሻለሁ” አላት። እርስዋም፥ “እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ ስጠኝ” አለችው። እርሱም፥ “ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርስዋም፥ “ቀለበትህን፥ ኩፌትህን፥ በእጅህ ያለውን በትር” አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ፤ እርስዋም ፀነሰችለት። እርስዋም ተነሥታ ሄደች፤ መጐናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነቷን ልብስ ለበሰች።
ዘፍጥረት 38:11-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት። ይህን ያለውም፣ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጕር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር፣ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች።
ዘፍጥረት 38:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይሁዳም ምራትን ትዕማርን፦ ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ዘመንም በኍላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች ይሁዳም ተጽናና የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ። ለትዕማርም፦ እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት። እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች ተሸፈነችም ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች ሴሌም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና። ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው ፊትዋን ተሸፍና ነበርና። ወደ እርስዋም አዘነበለ፦ እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም፦ ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው። የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም፦ እስክትሰደድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው። እርሱም፦ ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም፦ ቀለበትህን አምባርህን በእጅህ ያለውን በትር አለች እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ እርስዋም ፀነሰችለት። ኤስውም ተነሥታ ሄደች መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበስች።
ዘፍጥረት 38:11-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን “ልጄ ሴላ እስከሚያድግበት ጊዜ ድረስ ሂጂና በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ኑሪ” አላት። ይህንንም ያለው እንደ ወንድሞቹ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ነበር፤ ስለዚህ ትዕማር ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች። በርከት ካሉ ዓመቶች በኋላ የሴዋ ልጅ የሆነችው የይሁዳ ሚስት ሞተች፤ ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከወዳጁ ከዐዱላማዊው ከሒራ ጋር በጎቹን ወደሚሸልቱ ሰዎች ወደ ቲምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር “አማትሽ በጎቹን ለማሸለት ወደ ቲምና ይሄዳል” ብለው ነገሩአት። ስለዚህ ትዕማር የመበለትነት ልብሷን ለውጣ ፊቷን በሻሽ ሸፈነች፤ ወደ ቲምና በሚወስደው መንገድ ዳር በዔናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ይህንንም ያደረገችው ሴላ አድጎ ሳለ ለእርሱ በሚስትነት እንድትሰጥ አለመፈቀዱን ስለ ተረዳች ነው። ፊቷን በሻሽ ሸፍና ስለ ነበር ይሁዳ ባያት ጊዜ አመንዝራ ሴት መሰለችው። ምራቱ እንደ ሆነች ሳያውቅ እርስዋ ወደተቀመጠችበት ወደ መንገድ ዳር ወጣ አለና “እባክሽ ወደ አንች እንድገባ ፍቀጂልኝ” ብሎ ጠየቃት። እርስዋ “ፈቃድህን ብፈጽም ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። እርሱም “ከመንጋዎቼ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርስዋም “እሺ እንግዲያውስ ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ የሚሆን ነገር ስጠኝ” አለችው። እርሱም “ታዲያ፥ መያዣ የሚሆን ነገር ምን ልስጥሽ?” አላት። እርስዋም “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያውና ይህን የያዝከውን በትር ስጠኝ” አለችው። ስለዚህ የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና ወደ እርስዋ ገባ፤ እርስዋም ፀነሰችለት ከዚያ በኋላ ሻሽዋን ከፊቷ ላይ አንሥታ የመበለትነት ልብሷን እንደገና ለበሰች።
ዘፍጥረት 38:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፥ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፥ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፥ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጉር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር፥ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጉር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፥ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፥ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፥ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፥ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፥ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፥ “እባክሽ አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፥ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፥ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፥ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፥ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፥ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች።