ዘፍጥረት 35:9-13
ዘፍጥረት 35:9-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደገና በሎዛ ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም ባረከው። እግዚአብሔርም አለው፥ “ስምህ ያዕቆብ አይባል፤ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ” ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም አለው፥ “አምላክህ እኔ ነኝ፤ ብዛ፤ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፤ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
ዘፍጥረት 35:9-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም። እግዚአብሔርም፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው። ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ። ለአብርሃምና ለይሥሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔርም ከርሱ ጋራ ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
ዘፍጥረት 35:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርይ ከተመለስ በኍላ እንደ ገና ተገለጠለት ባረከውም። እግዚአብሔርም፦ ስምህ ያዕቆብ ነው ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር አለው፦ ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ ብዛ ተባዛም ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃም ለይስሐቅም የሰጠኍትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ ከአንተም በኍላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጠለሁ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
ዘፍጥረት 35:9-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው። ደግሞም “ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እስራኤል ትባላለህ እንጂ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም” አለው። ስለዚህም እግዚአብሔር ያዕቆብን “እስራኤል” ብሎ ጠራው። ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዙ ልጆች ይኑርህ፤ ዘርህም ይብዛ፤ የብዙ ሕዝብ አባት ሁን፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወለዱ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠሁትን ምድር ለአንተም እሰጥሃለሁ፤ ይህንኑ ምድር ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ከዚያ ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
ዘፍጥረት 35:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከፓዳን-ኣሪም ከተመለስ በኋላ እንደገና ተገለጠለት፥ ባረከውም። እግዚአብሔርም፦ “ስምህ ያዕቆብ ነው፥ ከእንግዲህም ወዲህ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ፥ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥” አለው። ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም አለው፦ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፥ ብዛ፥ ተባዛም፥ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጉልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጠለሁ።” እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።