ዘፍጥረት 32:22-26
ዘፍጥረት 32:22-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያችም ሌሊት ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ዕቁባቶቹን ዐሥራ አንዱንም ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። ወሰዳቸውም፤ ወንዙንም አሻገራቸው፤ ገንዘቡንም ሁሉ አሻገረ። ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ያዘው፤ የያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ። እንዲህም አለው፥ “ሊነጋ ጎሕ ቀድዶአልና ልቀቀኝ።” እርሱም “ከአልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።
ዘፍጥረት 32:22-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ። ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው ዐደረ። ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። በዚያን ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።
ዘፍጥረት 32:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያች ሌሊትም ተነሣ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንድንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው ከብቱን ሁሉ አሻገረ። ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ። እንዲህም አለው፦ ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም፦ ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።
ዘፍጥረት 32:22-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያኑ ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ ሁለቱን ሚስቶቹን፥ ሁለቱን ሴቶች አገልጋዮቹንና፥ ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። እነርሱን ካሻገረም በኋላ ያለውን ጓዝ ሁሉ አሻገረ። እርሱ ግን በስተማዶ ለብቻው ቀረ፤ ከዚህ በኋላ ሌሊቱ እስኪነጋ ድረስ አንድ ሰው ሲታገለው ዐደረ። ያ ሰው ያዕቆብን በትግል ማሸነፍ እንዳቃተው ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ መታው፤ ያዕቆብም በሚታገልበት ጊዜ ጭኑ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤ ከዚህ በኋላ ሰውየው “ሌሊቱ ሊነጋ ስለ ሆነ ልቀቀኝ” አለ። ያዕቆብም “ካልባረክኸኝ አለቅህም” አለው።
ዘፍጥረት 32:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹን፥ እና ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። እነርሱን ወስዶ ወንዙን አሻገራቸው፥ ያለውን ሁሉ እንደዚሁ አሻገረ። ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፥ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ሲታገለው አደረ። ያ ሰው ያዕቆብን እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ፥ የጭኑን ሹልዳ ነካው፥ ያዕቆብም ሲታገለው የጭኑ ሹልዳ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤። ከዚያ ሰውየው፦ “የንጋት ጎህ ሊቀድ ነውና ልቀቀኝ” አለው። እርሱም፦ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።