ዘፍጥረት 29:16-25
ዘፍጥረት 29:16-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱም ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች፥ ፊቷም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደዳት፤ ያዕቆብም ላባን እንዲህ አለው፥ “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ። ሚስት ትሆነኝ ዘንድ እርስዋን ስጠኝ” አለው። ላባም፥ “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለማውቅህ ለዘመዴ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለው። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፥ “እንግዲህ ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው።” ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ወደ ያዕቆብ አስገባት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። ላባም ለልጁ ልያ አገልጋዪቱን ዘለፋን አገልጋይ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ነበረች፤ ያዕቆብም ላባን፥ “ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ?” አለው።
ዘፍጥረት 29:16-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር። ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው። ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ ዐብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ለርሷ ካለው ፍቅር የተነሣ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው። ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቷል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው። ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ዐብሯት ተኛ። ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጥር እንድትሆን ሰጣት። ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጕድ ሠራኸኝ? ያገለገልሁህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው።
ዘፍጥረት 29:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደደ እንዲህም አለ፦ ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባር ዓመት እገዛልሃለሁ። ላባም፦ ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፦ ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው። ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እንሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም፦ ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለግልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው።
ዘፍጥረት 29:16-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ታላቂቱ ልያ፤ ታናሽቱ ራሔል ይባሉ ነበር። ልያ ዐይነ ልም ስትሆን፥ ራሔል ግን ቁመናዋ የሚያምር የደስ ደስ ያላት ነበረች። ያዕቆብ ራሔልን እጅግ ስለ ወደዳት “ራሔልን ብትድርልኝ ሰባት ዓመት አገለግልሃለሁ” አለ። ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ እሺ ተስማምቼአለሁ፤ እዚሁ ከእኔ ጋር ኑር” አለው። ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ይሁን እንጂ ራሔልን በጣም ይወዳት ስለ ነበር የቈየበት ጊዜ ጥቂት ቀን ብቻ መስሎ ታየው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ላባን “እነሆ፥ የአገልግሎት ዘመኔ ተፈጽሞአል፤ ሚስት እንድትሆነኝ ልጅህን ስጠኝ” አለው። ላባም የሠርግ ድግስ አዘጋጅቶ በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ጠራ። ነገር ግን በመሸ ጊዜ ላባ በራሔል ምትክ ልያን ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ወደ ልያ ገባ። ላባ ሴት አገልጋዩን ዚልፋን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለልያ ሰጣት። በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ልያ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ ወደ ላባ ሄዶ “ይህ ያደረግህብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ራሔልን ለማግኘት አልነበረምን? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?” አለው።
ዘፍጥረት 29:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፥ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፥ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፥ እንዲህም አለ፦ “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ።” ላባም፦ “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፥ ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለ። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፥ እርሷንም ይወድዳት ስለ ነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፦ “ወደ እርሷ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና” አለው። ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፥ ያዕቆብም ወደ እርሷ ገባ። ላባም ለልጁ ለልያ ባርያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፥ ላባንም፦ “ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለግልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ?” አለው።