ዘፍጥረት 24:12-19
ዘፍጥረት 24:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አለ፥ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፤ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሰዎች ሴቶች ልጆችም ውኃውን ሊቀዱ ይወጣሉ፤ እንስራሽን አዘንብለሽ ውኃ አጠጭኝ የምላት እርስዋም፦ ‘አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ እስኪረኩ አጠጣለሁ’ የምትለኝ ድንግል፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ለአብርሃም ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” እንደዚህ በልቡ ያሰበውን መናገሩን ሳይፈጽም እንዲህ ሆነ፦ የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት የሚልካ ልጅ የባቱኤል ሴት ልጅ ርብቃ እነሆ፥ መጣች፥ እንስራዋንም በጫንቃዋ ተሸክማ ነበር። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማታውቅ ድንግል ነበረች። ወደ ውኃው ጕድጓድም ወረደች፤ ውኃም ቀዳች፤ እንስራዋንም ሞልታ ወጣች። ያም ሰው ሊገናኛት ሮጠና፥ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ አጠጪኝ” አላት። እርስዋም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ በእጅዋ አውርዳ እስኪረካ አጠጣችው። እርሱንም ከአጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለችው።
ዘፍጥረት 24:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጕዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው። እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘ዕንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች። ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች።
ዘፍጥረት 24:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አለ፦ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ እለምንሃለሁ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዩ የምላት እርስዋም፦ አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና፦ ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። እርስዋም፦ ጌታዬ ሆይ ጠጣ አለችው ፈጥና፥ እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኍላ፦ ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች።
ዘፍጥረት 24:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አገልጋዩም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የእኔን ሐሳብ በመፈጸም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥ። እነሆ፥ እኔ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ ከእነርሱም አንድዋን ልጃገረድ ‘እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ’ እላታለሁ፤ ‘አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውሃ ቀድቼ አመጣለሁ’ ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የመረጥካት እርስዋ ትሁን፤ በዚህም ሁኔታ ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት በቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቈንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጒድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄደና “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርስዋም “እሺ ጌታዬ ጠጣ” አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። ጠጥቶም ከረካ በኋላ “ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ” አለችው።
ዘፍጥረት 24:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፥ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃ ሊቀዱ ይመጣሉ፥ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርሷም አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርሷ ለባርያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፥ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፥ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፥ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊያናግራት ሮጠና፦ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፥ ፈጥናም እንስራዋን በእጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለች።