ዘፍጥረት 21:14-19
ዘፍጥረት 21:14-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።
ዘፍጥረት 21:14-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱ ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሣ፤ ጥቂት ምግብ፥ ውሃም በአቁማዳ ሞልቶ ለአጋር ሰጣት፤ ልጁንም በጀርባዋ አሳዝሎ ከቤት አስወጣት፤ እርስዋም ከዚያ ወጥታ በቤርሳቤህ በረሓ ትንከራተት ጀመር። በአቁማዳ የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ ልጁን በቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው፤ እርስዋም “ልጄ ሲሞት ማየት አልፈልግም” በማለት ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያኽል ርቃ ተቀመጠች፤ እዚያም ሆና ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም ልጁ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን “አጋር ሆይ፤ የምትጨነቂበት ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የልጁን ለቅሶ ሰምቶአልና አይዞሽ አትፍሪ፤ ተነሺ፤ ሂጂና ልጁን አንሥተሽ ዕቀፊው የእርሱንም ዘር አበዛለሁ፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ” አላት። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ዐይኖችዋን ከፈተላትና አንድ የውሃ ጒድጓድ አየች፤ ሄዳም በአቁማዳው ውሃ ሞላች፤ ለልጅዋም አጠጣችው።
ዘፍጥረት 21:14-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፤ እንጀራንም ወሰደ፤ የውኃ አቍማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፤ ሕፃኑንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች፤ በዐዘቅተ መሐላም በኩል ባለው ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። ውኃውም ከአቍማዳው አለቀ፤ ሕፃኑንም ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር ጥላው ሄደች፤ ልጄ ሲሞት አላየውም ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ እየተመለከተች፥ ፊት ለፊት ተቀመጠች፤ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የሕፃኑን ጩኸት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የልጅሽን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፤ ልጅሽንም አንሺ፤ በእጅሽም አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ለአጋር ዐይንዋን ከፈተላት፤ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቍማዳውን በውኃ ሞላች፤ ልጅዋንም አጠጣችው።
ዘፍጥረት 21:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አብርሃምም ማልዶ ተነሣ እንጀራንም ወሰደ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትክሻው አሸከማት ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቀበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው እርስዋም ሄደች፥ ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ አጋር ሆይ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት የውኃ ጕድጓድንም አየች ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች ብላቴናውንም አጠጣች።
ዘፍጥረት 21:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፥ እርሷም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፥ ብላቴናውንም ከአንድ ቁጥቋጦ በታች ጣለችው፥ እርሷም ሄደች ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፥ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጉድጓድንም አየች፥ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።