ዘፍጥረት 14:17-20
ዘፍጥረት 14:17-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኮሎዶጎሞርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰም በኋላ የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሜዳ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። አብራምንም ባረከው፤ “አብራም ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም ቡሩክ ነው” አለው። አብራምም ከሁሉ ዐሥራትን ሰጠው።
ዘፍጥረት 14:17-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አብራም ኮሎዶጎምርንና አብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) አብራምን ይባርክ፤ ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣ ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ይባረክ።” አብራምም ካመጣው ሁሉ ዐሥራትን ሰጠው።
ዘፍጥረት 14:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለስ በኍላም የሰዶም ንጉሥ ሸለቆ በሆን በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። ባረከውም፤ አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።
ዘፍጥረት 14:17-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አብራም ከዶርላዖሜርና ከእነርሱ ጋር አብረው የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፥ የሰዶም ንጉሥ “የንጉሥ ሸለቆ” እየተባለ በሚጠራው በሻዌህ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ፤ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም ለአብራም እንጀራና የወይን ጠጅ አመጣለት፤ እንዲህ ብሎም አብራምን ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር አብራምን ይባርክ! በጠላቶችህ ላይ ድልን ያቀዳጀህ፥ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።” አብራምም በምርኮ ካገኘው ሀብት ሁሉ አንድ ዐሥረኛውን ለመልከ ጼዴቅ ሰጠው።
ዘፍጥረት 14:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፥ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። እንዲህም ሲል ባረከውም፦ አብራም ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፥ ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ፥ ልዑል እግዚአብሔርም ይባረክ፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።