ገላትያ 6:3-8
ገላትያ 6:3-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንዱም ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ለሌላ ያይደለ ለራሱ መመኪያ እንዲሆነው ሁሉም ሥራዉን ይመርምር። ሁሉም ሸክሙን ይሸከማልና። ይህንም ነገር ንኡሰ ክርስቲያን ይስማው፤ መልካሙንም ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ይማር። አያስቱአችሁ፤ በእግዚአብሔርም የሚዘብት አይኑር፤ ሰውም የሚዘራውን ያጭዳል። በሥጋው የሚዘራ ሞትን ያጭዳል፤ በመንፈሱም የሚዘራ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል።
ገላትያ 6:3-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና። ማንም ቃሉን የሚማር፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ከመምህሩ ጋር ይካፈል። አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል። ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።
ገላትያ 6:3-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።
ገላትያ 6:3-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ማንም ሰው ከሌሎች የሚሻልበት ነገር ሳይኖረው “እኔ ከሌሎች እበልጣለሁ” ብሎ ቢያስብ ራሱን ያታልላል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ መርምሮ ይፈትን፤ ከዚህ በኋላ ራሱን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ሳይሆን ለራሱ ብቻ የሚመካበትን ነገር ያገኛል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሸክም መሸከም አለበት። ቃሉን የሚማር ሰው ከአስተማሪው ጋር መልካሙን ነገር ሁሉ ይካፈል። ራሳችሁን አታታሉ፤ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ አትቀልዱ፤ ሥጋውን ለማስደሰት የሚዘራ ከሥጋው ሞትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ከመንፈስ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል።
ገላትያ 6:3-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንድ ሰው ምንም ሳይሆን አንድ ነገር የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። እያንዳንዱ የገዛ ሥራውን ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፥ ስለ ሌላው ግን አይደለም። እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማልና። ቃሉን የሚማር መልካሙን ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ጋር ይካፈል። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል።