የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ገላትያ 6:1-18

ገላትያ 6:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ ከእ​ና​ንተ ወገን የተ​ሳ​ሳተ ሰው ቢኖር በመ​ን​ፈስ ቅዱስ የጸ​ና​ችሁ እና​ንት እን​ዳ​ት​ሳ​ሳቱ ለራ​ሳ​ችሁ እየ​ተ​ጠ​በ​ቃ​ችሁ፥ እን​ደ​ዚህ ያለ​ውን ሰው ቅን​ነት ባለው ልቡና አጽ​ኑት። ከእ​ና​ንተ እያ​ን​ዳ​ንዱ የባ​ል​ን​ጀ​ራ​ውን ሸክም ይሸ​ከም፤ በዚ​ህም የክ​ር​ስ​ቶ​ስን ሕግ ትፈ​ጽ​ማ​ላ​ችሁ። አን​ዱም ምንም ሳይ​ሆን ምንም የሆነ ቢመ​ስ​ለው ራሱን ያታ​ል​ላ​ልና። ለሌላ ያይ​ደለ ለራሱ መመ​ኪያ እን​ዲ​ሆ​ነው ሁሉም ሥራ​ዉን ይመ​ር​ምር። ሁሉም ሸክ​ሙን ይሸ​ከ​ማ​ልና። ይህ​ንም ነገር ንኡሰ ክር​ስ​ቲ​ያን ይስ​ማው፤ መል​ካ​ሙ​ንም ነገር ሁሉ ከሚ​ያ​ስ​ተ​ም​ረው ይማር። አያ​ስ​ቱ​አ​ችሁ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ዘ​ብት አይ​ኑር፤ ሰውም የሚ​ዘ​ራ​ውን ያጭ​ዳል። በሥ​ጋው የሚ​ዘራ ሞትን ያጭ​ዳል፤ በመ​ን​ፈ​ሱም የሚ​ዘራ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን ያጭ​ዳል። በጎ ሥራ መሥ​ራ​ትን ቸል አን​በል፥ በጊ​ዜው እና​ገ​ኘ​ዋ​ለ​ንና። እን​ግ​ዲህ ጊዜ ሳለን ለሁሉ መል​ካም ሥራ እና​ድ​ርግ፤ ይል​ቁ​ንም ለሃ​ይ​ማ​ኖት ሰዎች። በእጄ እንደ ጻፍ​ሁ​ላ​ችሁ እዩ። ለሰው ፊት ሊያ​ደሉ የሚ​ወዱ እነ​ዚያ እን​ድ​ት​ገ​ዘሩ ያስ​ገ​ድ​ዱ​አ​ች​ኋል፤ ነገር ግን የክ​ር​ስ​ቶ​ስን መስ​ቀል እን​ዳ​ት​ከ​ተሉ ነው። የተ​ገ​ዘ​ሩ​ትም ቢሆኑ በሰ​ው​ነ​ታ​ችሁ እን​ደ​ም​ት​መኩ ልት​ገ​ዘሩ ይወ​ዳሉ እንጂ ኦሪ​ትን አል​ጠ​በ​ቁም። እኔ ግን በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ መስ​ቀል እንጂ በሌላ አል​መ​ካም፤ በእኔ ዘንድ ዓለሙ የሞተ ነው፥ እኔም በዓ​ለሙ ዘንድ የሞ​ትሁ ነኝ። በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ዘንድ አዲስ ፍጥ​ረት መሆን ነው እንጂ መገ​ዘር አይ​ጠ​ቅ​ምም፤ አለ​መ​ገ​ዘ​ርም ግዳጅ አይ​ፈ​ጽ​ምም። ይህን ሕግ ለሚ​ፈ​ጽሙ ሰዎች ሰላ​ምና ይቅ​ርታ ይሁን፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወገ​ኖች በሆኑ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይም ይሁን። እን​ግ​ዲህ ወዲ​ህስ የሚ​ያ​ደ​ክ​መኝ አይ​ኑር፤ እኔ የኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን መከራ በሥ​ጋዬ እሸ​ከ​ማ​ለሁ። ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ የጌ​ታ​ችን የኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ጸጋ ከእ​ና​ንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲቶ እጅ ወደ ገላ​ትያ ሰዎች የተ​ላ​ከች መል​እ​ክት ተፈ​ጸ​መች። ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ጋና ይሁን፤ አሜን።

ገላትያ 6:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና። ማንም ቃሉን የሚማር፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ከመምህሩ ጋር ይካፈል። አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል። ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን። ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ ተመልከቱ። ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ትገረዙ ዘንድ ሊያስገድዷችሁ ይጥራሉ፤ ይህንም የሚያደርጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ነው። እነርሱ በሥጋችሁ ለመመካት ሲሉ እንድትገረዙ ፈለጉ እንጂ፣ የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን የሚጠብቁ አይደሉም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር፣ ሌላው ትምክሕት ከእኔ የራቀ ይሁን። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። ይህን ትእዛዝ በሚከተሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በሆነው እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ገላትያ 6:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ። ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ገላትያ 6:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞች ሆይ! ሰው ተሳስቶ አንዳች ጥፋት አድርጎ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁት እናንተ እንዲህ ዐይነቱን ሰው በገርነት አቅኑት፤ ነገር ግን አንተም በዚህ ዐይነት ፈተና እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህ ዐይነት የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። ማንም ሰው ከሌሎች የሚሻልበት ነገር ሳይኖረው “እኔ ከሌሎች እበልጣለሁ” ብሎ ቢያስብ ራሱን ያታልላል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ መርምሮ ይፈትን፤ ከዚህ በኋላ ራሱን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ሳይሆን ለራሱ ብቻ የሚመካበትን ነገር ያገኛል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሸክም መሸከም አለበት። ቃሉን የሚማር ሰው ከአስተማሪው ጋር መልካሙን ነገር ሁሉ ይካፈል። ራሳችሁን አታታሉ፤ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ አትቀልዱ፤ ሥጋውን ለማስደሰት የሚዘራ ከሥጋው ሞትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ከመንፈስ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል። ተስፋ ካልቈረጥን ወቅቱ ሲደርስ መከር ስለምንሰበስብ መልካም ሥራን ከመሥራት አንስነፍ። ምቹ ጊዜ ካገኘን ለሰዎች ሁሉ ይልቁንም ለሚያምኑ ቤተ ሰዎች መልካም ነገርን እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደሎች ይህን በእጄ እንደ ጻፍኩላችሁ ተመልከቱ! እንድትገረዙ የሚያስገድዱአችሁ በውጭ መልካም መስለው ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ይህን የሚያደርጉትም በክርስቶስ መስቀል ምክንያት ስደት እንዳይደርስባቸው ብለው ነው። እነርሱ በእናንተ ሥጋ ለመመካት ብለው እንድትገረዙ ይፈልጋሉ እንጂ የተገረዙትም እንኳ ራሳቸው ሕግን አይፈጽሙም። ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ መመካት ከእኔ ይራቅ፤ በዚህም መስቀል ዓለም ከእኔ ተለይቶአል፤ እኔም ከዓለም ተለይቼአለሁ። ስለዚህ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤ የሚጠቅመውስ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። ይህን መመሪያ ለሚከተሉ ሁሉና የእግዚአብሔር ወገኖች ለሆኑት እስራኤላውያን ሰላምና ምሕረት ይሁን። በሰውነቴ ላይ ያለው የግርፋት ምልክት የኢየሱስ አገልጋይ መሆኔን ስለሚያመለክት ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን! አሜን።

ገላትያ 6:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞች ሆይ! ሰው ማንኛውንም ኃጢአት አድርጎ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። የእርስ በርሳችሁን ሸክም ተሸከሙ፥ በዚህም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን አንድ ነገር የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። እያንዳንዱ የገዛ ሥራውን ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፥ ስለ ሌላው ግን አይደለም። እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማልና። ቃሉን የሚማር መልካሙን ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ጋር ይካፈል። አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል። መልካምን ሥራ ለመሥራት አንታክት፥ ካልዛልን ወቅቱ በደረሰ ጊዜ እናጭዳለንና። ስለዚህ ጊዜ ሳለን ለሰው ሁሉ፥ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። በሥጋ መልካም ሆነው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ እንድትገረዙ አስገደዱአችሁ፤ ይህን ያደረጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም፥ ነገር ግን በሥጋችሁ እንዲመኩ እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። ለእኔ ግን፥ ዓለም ለእኔ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት አይሁንብኝ። አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ፥ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ እና በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ምልክት በሰውነቴ ላይ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ገላትያ 6:1-18

ገላትያ 6:1-18 NASVገላትያ 6:1-18 NASV