ገላትያ 5:7-15
ገላትያ 5:7-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቀድሞስ በመልካም ተፋጥናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና። ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግዝረትን ገና የምሰብክ ከሆነ፥ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል። የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ። “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና። እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:7-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።” የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ፤ እስከ ዛሬ ስለ መገረዝ የምሰብክ ከሆነ፣ ታዲያ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ፣ መስቀል ዕንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። ግራ የሚያጋቧችሁ ሰዎች የራሳቸውን መግረዝ ብቻ ሳይሆን ይጐንድሉ! ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:7-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደኅና ትራመዱ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለእውነት እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ዐይነቱ ምክር ከጠራችሁ ከእግዚአብሔር የመጣ አይደለም። ይህም “ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ ያቦካዋል” እንደሚባለው ነው። ነገር ግን ከዚህ የተለየ ሌላ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እርግጠኛ ሆኜ በጌታ እተማመናለሁ፤ ማንም ግራ የሚያጋባችሁ ቢኖር ቅጣቱን ይቀበላል። ወንድሞቼ ሆይ! እኔ እስከ አሁን የምሰብከው “ለመዳን መገረዝ ያስፈልጋል” እያልኩ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኝ ነበር? እንዲህ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ መስቀል ለሰዎች እንቅፋት መሆኑ ይቀር ነበር። እንግዲህ እነዚህ ግራ የሚያጋቡአችሁ ሰዎች ቢፈልጉ መገረዝ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ጃንደረባ ቢያደርጉ እወድ ነበር። ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። ሌላ ነገር እንደማታስቡ ስለ እናንተ በጌታ እተማመናለሁ፤ የሚያውካችሁ፥ ማንም ቢሆን ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ! እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ ኖሮ ታዲያ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? ስለዚህ የመስቀል እንቅፋትነት ይቀር ነበር። የሚያውኩአችሁ ራሳቸውን ይስለቡ! ወንድሞች ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁ ለሥጋ ብቻ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር አንዳችሁ ለሌላችሁ ባርያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተፈጽሟል፥ እርሱም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።