የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ገላትያ 5:5-26

ገላትያ 5:5-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እኛ ግን በመ​ን​ፈስ ቅዱስ፥ በእ​ም​ነ​ትም ልን​ጸ​ድቅ ተስፋ እና​ደ​ር​ጋ​ለን። በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ዘንድ በፍ​ቅር የም​ት​ሠራ እም​ነት እንጂ መገ​ዘር አይ​ጠ​ቅ​ም​ምና፤ አለ​መ​ገ​ዘ​ርም ግዳጅ አይ​ፈ​ጽ​ም​ምና። ቀድ​ሞስ በመ​ል​ካም ተፋ​ጥ​ና​ችሁ ነበር፤ በእ​ው​ነት እን​ዳ​ታ​ምኑ ማን አሰ​ና​ከ​ላ​ችሁ? ይህ መፋ​ጠ​ና​ችሁ ከሚ​ጠ​ራ​ችሁ አይ​ደ​ለ​ምና። ጥቂት እርሾ ብዙ​ውን ዱቄት መጻጻ ያደ​ር​ገው የለ​ምን? እኔ ሌላ እን​ዳ​ታ​ስቡ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ አም​ኛ​ችሁ ነበር፤ የሚ​ያ​ው​ካ​ችሁ ግን የሆ​ነው ቢሆን ፍዳ​ውን ይሸ​ከ​ማል። ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ እኔ ግዝ​ረ​ትን ገና የም​ሰ​ብክ ከሆነ፥ እን​ግ​ዲህ ለምን ያሳ​ድ​ዱ​ኛል? እን​ግ​ዲህ የክ​ር​ስ​ቶስ የመ​ስ​ቀሉ ተግ​ዳ​ሮት እን​ዲ​ያው ቀር​ቶ​አል። የሚ​ያ​ው​ኩ​አ​ች​ሁም ሊለዩ ይገ​ባል። ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ እና​ን​ተስ ለነ​ጻ​ነት ተጠ​ር​ታ​ች​ኋል፤ ነገር ግን በሥ​ጋ​ችሁ ፈቃድ ለነ​ጻ​ነ​ታ​ችሁ ምክ​ን​ያት አታ​ድ​ር​ጉ​ላት፤ ለወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ሁም በፍ​ቅር ተገዙ። “ወን​ድ​ም​ህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚ​ለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈ​ጽ​ማ​ልና። እርስ በር​ሳ​ችሁ የም​ት​በ​ላ​ሉና የም​ት​ነ​ካ​ከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በር​ሳ​ችሁ እን​ዳ​ት​ተ​ላ​ለቁ ተጠ​ን​ቀቁ። እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ በመ​ን​ፈስ ኑሩ እንጂ የሥ​ጋ​ች​ሁን ፈቃድ አታ​ድ​ርጉ። ሥጋ መን​ፈስ የማ​ይ​ሻ​ውን ይሻ​ልና፥ መን​ፈ​ስም ሥጋ የማ​ይ​ሻ​ውን ይሻ​ልና፥ የም​ት​ሹ​ት​ንም እን​ዳ​ታ​ደ​ርጉ እርስ በር​ሳ​ቸው ይጣ​ላሉ። የመ​ን​ፈ​ስን ፈቃድ የም​ት​ከ​ተሉ ከሆ​ና​ችሁ፥ ከኦ​ሪት ወጥ​ታ​ች​ኋል። የሥ​ጋም ሥራው ይታ​ወ​ቃል፤ እር​ሱም ዝሙት፥ ርኵ​ሰት፥ መዳ​ራት፥ ጣዖት ማም​ለክ፥ ሥራይ ማድ​ረግ፥ መጣ​ላት፥ ኵራት፥ የም​ን​ዝር ጌጥ፥ ቅናት፥ ቍጣ፥ ጥር​ጥር፥ ፉክ​ክር፥ ምቀ​ኝ​ነት፥ መጋ​ደል፥ ስካር ይህ​ንም የመ​ሰለ ሁሉ ነው። አስ​ቀ​ድሜ እንደ ነገ​ር​ኋ​ችሁ ይህን የሚ​ያ​ደ​ርግ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥት አያ​ይም። የመ​ን​ፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕ​ግ​ሥት፥ ምጽ​ዋት፥ ቸር​ነት፥ እም​ነት፥ ገር​ነት፥ ንጽ​ሕና ነው። ከዚህ ሕግ የሚ​በ​ልጥ የለም። በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ያመኑ ግን ሰው​ነ​ታ​ቸ​ውን ከም​ኞ​ትና ከኀ​ጢ​አት ለዩ። አሁ​ንም በመ​ን​ፈስ እን​ኑር፤ በመ​ን​ፈ​ስም እን​መ​ላ​ለስ። ኩሩ​ዎች አን​ሁን፤ እርስ በር​ሳ​ችን አን​ተ​ማማ፤ እርስ በር​ሳ​ች​ንም አን​ቀ​ናና።

ገላትያ 5:5-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን ጽድቅ፣ በመንፈስ አማካይነት በእምነት ሆነን በናፍቆት እንጠባበቃለን። በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑ፣ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፤ የሚጠቅመውስ በፍቅር የሚገለጽ እምነት ብቻ ነው። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።” የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ፤ እስከ ዛሬ ስለ መገረዝ የምሰብክ ከሆነ፣ ታዲያ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ፣ መስቀል ዕንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። ግራ የሚያጋቧችሁ ሰዎች የራሳቸውን መግረዝ ብቻ ሳይሆን ይጐንድሉ! ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ እላለሁ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን፣ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን ይመኛልና፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ፣ የምትፈልጉትን አታደርጉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፣ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። አስቀድሜ እንዳልሁ፣ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተጐነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።

ገላትያ 5:5-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

ገላትያ 5:5-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እኛ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የጽድቅን ተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚኖር በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም ጥቅም አይሰጠውም። ደኅና ትራመዱ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለእውነት እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ዐይነቱ ምክር ከጠራችሁ ከእግዚአብሔር የመጣ አይደለም። ይህም “ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ ያቦካዋል” እንደሚባለው ነው። ነገር ግን ከዚህ የተለየ ሌላ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እርግጠኛ ሆኜ በጌታ እተማመናለሁ፤ ማንም ግራ የሚያጋባችሁ ቢኖር ቅጣቱን ይቀበላል። ወንድሞቼ ሆይ! እኔ እስከ አሁን የምሰብከው “ለመዳን መገረዝ ያስፈልጋል” እያልኩ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኝ ነበር? እንዲህ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ መስቀል ለሰዎች እንቅፋት መሆኑ ይቀር ነበር። እንግዲህ እነዚህ ግራ የሚያጋቡአችሁ ሰዎች ቢፈልጉ መገረዝ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ጃንደረባ ቢያደርጉ እወድ ነበር። ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ በመንፈስ ተመርታችሁ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ። የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ይቃረናል፤ መንፈስና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዢዎች አትሆኑም። የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነርሱም ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ስድነት ጣዖትን ማምለክ፥ ሟርት፥ ጠላትነት፥ ንትርክ፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ መለያየት፥ አድመኛነት፥ ምቀኝነት፥ ስካር፥ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፤ ከዚህ በፊት እንዳስጠነቀቅኋችሁ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንደ እነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ደግነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ ገርነት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚቃረን ሕግ የለም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑት ሰዎች ሥጋን ከፍትወቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ እንመራ። አንዱ ሌላውን ለክፉ በማነሣሣት እርስ በእርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

ገላትያ 5:5-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እኛ በመንፈስ፥ በእምነት፥ የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ በክርስቶስ ኢየሱስ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። ሌላ ነገር እንደማታስቡ ስለ እናንተ በጌታ እተማመናለሁ፤ የሚያውካችሁ፥ ማንም ቢሆን ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ! እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ ኖሮ ታዲያ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? ስለዚህ የመስቀል እንቅፋትነት ይቀር ነበር። የሚያውኩአችሁ ራሳቸውን ይስለቡ! ወንድሞች ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁ ለሥጋ ብቻ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር አንዳችሁ ለሌላችሁ ባርያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተፈጽሟል፥ እርሱም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ይህን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን ይመኛል፥ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚቀዋወሙ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፥ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም ግልጽ ነው፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኩሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ አስማት፥ ጠላትነት፥ ጠብ፥ ቅናት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ መሶልሶል፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ፥ አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደ እነዚህ ያሉትን የሚቃረን ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተተነኳኮስንና እርስ በርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።