ገላትያ 5:13-25
ገላትያ 5:13-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ፥ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ። “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና። እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ። እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ። ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና፥ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና፥ የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ፥ ከኦሪት ወጥታችኋል። የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖት ማምለክ፥ ሥራይ ማድረግ፥ መጣላት፥ ኵራት፥ የምንዝር ጌጥ፥ ቅናት፥ ቍጣ፥ ጥርጥር፥ ፉክክር፥ ምቀኝነት፥ መጋደል፥ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው። አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ምጽዋት፥ ቸርነት፥ እምነት፥ ገርነት፥ ንጽሕና ነው። ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም። በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ። አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ።
ገላትያ 5:13-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ እላለሁ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን፣ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን ይመኛልና፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ፣ የምትፈልጉትን አታደርጉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፣ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። አስቀድሜ እንዳልሁ፣ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ።
ገላትያ 5:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።
ገላትያ 5:13-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ በመንፈስ ተመርታችሁ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ። የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ይቃረናል፤ መንፈስና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዢዎች አትሆኑም። የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነርሱም ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ስድነት ጣዖትን ማምለክ፥ ሟርት፥ ጠላትነት፥ ንትርክ፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ መለያየት፥ አድመኛነት፥ ምቀኝነት፥ ስካር፥ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፤ ከዚህ በፊት እንዳስጠነቀቅኋችሁ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንደ እነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ደግነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ ገርነት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚቃረን ሕግ የለም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑት ሰዎች ሥጋን ከፍትወቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ እንመራ።
ገላትያ 5:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁ ለሥጋ ብቻ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር አንዳችሁ ለሌላችሁ ባርያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተፈጽሟል፥ እርሱም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ይህን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን ይመኛል፥ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚቀዋወሙ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፥ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም ግልጽ ነው፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኩሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ አስማት፥ ጠላትነት፥ ጠብ፥ ቅናት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ መሶልሶል፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ፥ አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደ እነዚህ ያሉትን የሚቃረን ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።