ገላትያ 5:1-15
ገላትያ 5:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም።” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም እንደሚገባው እመሰክራለሁ። በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል። እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ፥ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ እናደርጋለን። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና። ቀድሞስ በመልካም ተፋጥናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና። ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግዝረትን ገና የምሰብክ ከሆነ፥ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል። የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ። “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና። እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። የምለውን አስተውሉ፤ ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንት እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ። መገረዝ ለሚፈልግ ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት እንደ ገና ለእያንዳንዱ በግልጽ እናገራለሁ። በሕግ ለመጽደቅ የምትጥሩ፣ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋ ርቃችኋል። እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን ጽድቅ፣ በመንፈስ አማካይነት በእምነት ሆነን በናፍቆት እንጠባበቃለን። በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑ፣ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፤ የሚጠቅመውስ በፍቅር የሚገለጽ እምነት ብቻ ነው። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።” የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ፤ እስከ ዛሬ ስለ መገረዝ የምሰብክ ከሆነ፣ ታዲያ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ፣ መስቀል ዕንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። ግራ የሚያጋቧችሁ ሰዎች የራሳቸውን መግረዝ ብቻ ሳይሆን ይጐንድሉ! ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፦ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። እነሆ! እኔ ጳውሎስ የምላችሁ ይህ ነው፤ “መገረዝ ያስፈልገናል” ብላችሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም፤ “መገረዝ ያስፈልገኛል” ብሎ የሚገረዝ ሁሉ “ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት” ብዬ እንደገና አስጠነቅቀዋለሁ። እናንተ ሕግን በመጠበቅ ለመጽደቅ የምትፈልጉ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋውም ርቃችኋል። እኛ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የጽድቅን ተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚኖር በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም ጥቅም አይሰጠውም። ደኅና ትራመዱ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለእውነት እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ዐይነቱ ምክር ከጠራችሁ ከእግዚአብሔር የመጣ አይደለም። ይህም “ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ ያቦካዋል” እንደሚባለው ነው። ነገር ግን ከዚህ የተለየ ሌላ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እርግጠኛ ሆኜ በጌታ እተማመናለሁ፤ ማንም ግራ የሚያጋባችሁ ቢኖር ቅጣቱን ይቀበላል። ወንድሞቼ ሆይ! እኔ እስከ አሁን የምሰብከው “ለመዳን መገረዝ ያስፈልጋል” እያልኩ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኝ ነበር? እንዲህ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ መስቀል ለሰዎች እንቅፋት መሆኑ ይቀር ነበር። እንግዲህ እነዚህ ግራ የሚያጋቡአችሁ ሰዎች ቢፈልጉ መገረዝ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ጃንደረባ ቢያደርጉ እወድ ነበር። ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
ገላትያ 5:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በነጻነት እንድንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በባርነት ቀንበር እንደገና አትያዙ። እነሆ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፥ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። የተገረዘ ሰው ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት ብዬ ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፥ ከጸጋውም ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ፥ በእምነት፥ የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ በክርስቶስ ኢየሱስ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም። ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። ሌላ ነገር እንደማታስቡ ስለ እናንተ በጌታ እተማመናለሁ፤ የሚያውካችሁ፥ ማንም ቢሆን ፍርዱን ይቀበላል። ወንድሞች ሆይ! እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ ኖሮ ታዲያ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? ስለዚህ የመስቀል እንቅፋትነት ይቀር ነበር። የሚያውኩአችሁ ራሳቸውን ይስለቡ! ወንድሞች ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁ ለሥጋ ብቻ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር አንዳችሁ ለሌላችሁ ባርያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተፈጽሟል፥ እርሱም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።