ገላትያ 3:7-14
ገላትያ 3:7-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ያመኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቃቸው መጽሐፍ አስቀድሞ ገልጦአልና፤ አሕዛብም ሁሉ በእርሱ እንዲባረኩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋ ሰጠው። አሁንም የሚያምኑ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። በኦሪት ሕግ ያሉ ሁሉ በእርግማን ውስጥ ይኖራሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በዚህ በኦሪት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ የማይፈጽምና የማይጠብቅ ርጉም ይሁን።” የኦሪትን ሥራ በመሥራትስ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደማይጸድቁ ይታወቃል፤ “ጻድቅ ግን በእምነት ይድናል” ተብሎ ተጽፎአል። ኦሪትስ ሠርቶ የፈጸመ ይኖርበታል እንጂ በእምነት የሚያጸድቅ አይደለም። እኛንስ ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን መርገም በመሸከሙ ከኦሪት መርገም ዋጅቶናል፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው።” እኛ በክርስቶስ አምነን የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ እንድናገኝ የአብርሃም በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አሕዛብ ይመለስ ዘንድ።
ገላትያ 3:7-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እነዚያ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ አስተውሉ። መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው። ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋር ቡሩካን ናቸው። ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጻሕፍት የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏልና። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው። ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “ሕግጋትን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራል” ተብሏል። “በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤ ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።
ገላትያ 3:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን፦ የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
ገላትያ 3:7-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ የሚያምኑ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ዕወቁ። እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ ቅዱስ መጽሐፍ አስቀድሞ አይቶ “ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት አስቀድሞ ለአብርሃም የምሥራቹን ቃል አብሥሮአል። ስለዚህ የሚያምኑ ሁሉ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። “በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ትእዛዞች ሁሉ ጸንቶ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ “ሕግን በመፈጸም እንጸድቃለን” የሚሉ ሁሉ የተረገሙ ናቸው። “ጻድቅ ሰው ግን በእምነት ሕይወትን ያገኛል” ተብሎ ስለ ተጻፈ ሕግን በመፈጸም ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ እንዲያውም “ሰው በሕግ ሊኖር የሚችለው የሕግ ትእዛዞችን ሁሉ ሲፈጽም ነው” ተብሎ ተጽፎአል። “በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ ክርስቶስ ስለ እኛ እንደ ተረገመ ሰው ሆኖ ሕግ ከሚያስከትለው ርግማን ዋጀን። ይህም የሆነው እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለአሕዛብ እንዲደርስና እኛም እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ያለውን መንፈስ ቅዱስን በእምነት እንድንቀበል ነው።
ገላትያ 3:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ እነዚህ የሚያምኑት፥ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” ብሎ አስቀድሞ ለአብርሃም ወንጌልን ሰበከለት። ስለዚህም የሚያምኑት ከታመነው ከአብርሃም ጋር ተባርከዋል። ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ይሁን፤” ተብሎ ተጽፎአልና። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሏልና፥ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግ ከእምነት አይደለም፤ ነገር ግን “የሚፈጽማቸው በእነርሱ ይኖራል።” ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ፥ ከሕግ እርግማን ዋጅቶናል፤ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፤” ተብሎ ተጽፎአልና ይህም የአብርሃም በረከት፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ አሕዛብ እንዲደርስና የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል ነው።