ገላትያ 3:15-20
ገላትያ 3:15-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እንናገራለን፤ ሰውም እንኳን የጸናውን ኪዳን አይንቅም አይጨምርበትምም። እግዚአብሔርም ለአብርሃም፥ “ለአንተና ለዘርህ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፤ ለብዙዎች እንደሚናገር አድርጎ ለአንተና ለዘሮችህ አላለውም፤ ለአንድ እንደሚናገር አድርጎ፥ “ለዘርህ” አለው እንጂ ይኸውም ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እንዲህ እላለሁ፦ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ይህ ኪዳን ጽኑዕ ነው፤ ከዚህም በኋላ በአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኦሪት መጣች፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል አይደለም። መውረስ የኦሪትን ሕግ በመሥራት ከሆነ እንግዲህ በሰጠው ተስፋ አይደለማ፤ እነሆ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋውን ሰጠው። ታዲያ ኦሪት ለምን ተሠራች? ኦሪትስ ኀጢአትን ታበዛት ዘንድ፥ ተስፋ ያደረገለት ያ ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ በመላእክት በኩል በመካከለኛው እጅ ወረደች። መካከለኛው ግን ማንም አይደለም፤ አንድ እግዚአብሔር ነው እንጂ።
ገላትያ 3:15-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በእርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጕዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው። የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። የምለው እንዲህ ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም። ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል። ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር። ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ገላትያ 3:15-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ገላትያ 3:15-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! እስቲ ይህን ነገር በሰው ዘንድ ከተለመደ ነገር ጋር አነጻጽሩት፤ አንድ ሰው የገባው ቃል ኪዳን እንኳ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሰው ሊሽረው ወይም ሊጨምርበት አይችልም። እግዚአብሔርም ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋ ቃል የሰጠው በዚህ ዐይነት ነው፤ መጽሐፍ የተስፋ ቃል ከአብርሃም በኋላ የተሰጠው ለብዙዎች እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘርህ” ይላል፤ ይህም “ዘርህ” የተባለው ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እኔ የምለው ይህን ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ ቀደም ብሎ በእግዚአብሔር ተረጋግጦ የተሰጠውን ቃል ኪዳን በመሻር የተስፋውን ቃል ሊያጠፋው አይችልም። አንድ ነገር የሚወረሰው በሕግ አማካይነት ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል አማካይነት መሆኑ በቀረ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ውርስን ለአብርሃም የሰጠው በተስፋው ቃል አማካይነት ነው። ታዲያ፥ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ለአብርሃም በተስፋ የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ ክፉ ሥራ ምን መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ሕጉ በሥራ ላይ የዋለው በመላእክት ተሰጥቶ በአንድ ሰው አማካይነት ነው። ይሁን እንጂ በመካከል ሆኖ የሚያስታርቅ ሰው ለሁለት ወገን ነው እንጂ ለአንድ ወገን ብቻ አይሠራም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ገላትያ 3:15-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የጸና ኪዳን፥ የሰው ስንኳ ቢሆን፥ ማንም አያፈርሰውም ወይም አይጨምርበትም። የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር። ለብዙዎች እንደሆነ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደሆነ “ለዘርህም” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ይህንም እላለሁ፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የመጣው ሕግ፥ የተስፋውን ቃል ለማስቀረት፥ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን ሊሽር አይችልም። ውርስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፥ በተስፋ ቃል መሆኑ ይቀር ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም በተስፋ ቃል አማካይነት ሰጠው። ታዲያ ሕግ ለምንድን ነው? በተስፋ ቃል የተነገረው ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ ስለ መተላለፍ ተጨመረ፤ በመላእክት በኩል መካከለኛ እጅ ታዘዘ። መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።