ሕዝቅኤል 45:7-12
ሕዝቅኤል 45:7-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፤ የሕዝቤ አለቆችም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም።” ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል አለቆች ሆይ! ይብቃችሁ፤ ግፍንና ዐመፅን አስወግዱ፤ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እውነተኛ ሚዛን፥ እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ፥ እውነተኛም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። እንዲሁም የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ፥ የቆሮስ መስፈሪያ ዐሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ ዐሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። ሰቅሉም ሃያ አቦሊ ይሁን፤ ሃያ ሰቅል፥ ሃያ አምስት ሰቅል፥ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ።
ሕዝቅኤል 45:7-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ገዥው ከቅዱሱ ስፍራና ከከተማው ወሰን ግራና ቀኝ ርስት ይኖረዋል፤ ይህም ከምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ምሥራቅ በመዝለቅ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለውን ወሰን ርዝመት ተከትሎ ለአንዱ ነገድ ከተሰጠው ርስት ጋር ጐን ለጐን ይሄዳል። ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዥው ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዥዎቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል። “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ። የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው። አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ አምስት ሰቅልና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል።
ሕዝቅኤል 45:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፥ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፥ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፥ አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ፥ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፥ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፥ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን፥ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ።
ሕዝቅኤል 45:7-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሀገሪቱም መሪ ድርሻ ከተቀደሰው ቦታና ከከተማው ክልል ቀጥሎ በሁለቱም በኩል ማለትም በስተምዕራብ እስከ ሀገሪቱ ድንበር ሲደርስ በስተ ምሥራቅም እስከ ሀገሪቱ ድንበር የሚደርስ ይከለላል፤ ርዝመቱም ለአንድ ነገድ የሚደርሰውን ድርሻ ያኽላል። ይህም ክልል በእስራኤል ምድር መሪ ለሚሆነው መስፍን የርስት ድርሻ ይሆናል፤ ከዚህም በኋላ መሪዎች ሁሉ ሕዝቡን መጨቈን የለባቸውም፤ ነገር ግን ከሀገሪቱ ቀሪውን ምድር በሙሉ ለእስራኤል ነገዶች መተው ይኖርባቸዋል። ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የእስራኤል መሪዎች! እነሆ ለረጅም ጊዜ ኃጢአት ስትሠሩ ኖራችኋል፤ አሁን ግን ግፍንና ጭቈናን አቁሙ! ቅንና ትክክል የሆነውን ነገር ሥሩ! ሕዝቤ እንደገና ከምድራቸው ተፈናቅለው እንዲባረሩ አታድርጉ! ይህን የምነግራችሁ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። “እያንዳንዱ ሰው ትክክለኛ ሚዛንና መለኪያ እንዲሁም እኩል የሆነ መስፈሪያ ይኑረው። “የመስፈሪያዎች ሁሉ አማካኝ መለኪያ ጎሞር ይሁን፤ የደረቅ ነገሮች መስፈሪያ የሆነው ኢፍ፥ የፈሳሽ ነገሮች መለኪያ ከሆነው ባት ጋር እኩል መሆን አለበት፤ በዚህም ዐይነት አንድ ጎሞር ከዐሥር ኤፋና ከዐሥር ባት ጋር እኩል ይሆናል። “ሚዛናችሁም፥ ኻያ ጌራህ አንድ ሰቅል፥ ሥልሳ ሰቅል አንድ ምናን ይሁን፤
ሕዝቅኤል 45:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለአለቃውም የሚሆነው የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በጎንና በጎን ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። ይህም ከምድሪቱ በእስራኤል ዘንድ ርስት ይሆንለታል፥ መሪዎቼ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም፥ ነገር ግን ምድሪቱን ለእስራኤል ቤት እንደ ነገዳቸው ይሰጡአቸዋል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል መሪዎች ሆይ፥ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ጭቆናን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አንሱ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እውነተኛ ሚዛን እውነተኛ የኢፍ መስፈሪያና እውነተኛው የባዶስ መስፈሪያ ይኑራችሁ። የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ ይሁን። መለኪያው የቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። አንድ ሰቅል ሀያ ጌራህ ይሆናል፤ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል እና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር፥ አንድ ምናን ይሁንላችሁ።