ሕዝቅኤል 39:21-29
ሕዝቅኤል 39:21-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ክብሬንም እሰጣችኋለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። ከዚች ቀን ጀምሮ ለዘለዓለም የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኀጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ ከዱኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ መለስሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ። እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ መለስሁ። “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም። ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከአሕዛብም ሀገሮች በሰበሰብኋቸው ጊዜ፥ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አላስቀርም፤ ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልመልስም፤ መዓቴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 39:21-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር፣ አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። አሕዛብም የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ታማኞች ባለመሆን ከሠሩት ኀጢአት የተነሣ እንደ ተሰደዱ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። እንደ ርኩሰታቸውና እንደ በደላቸው መጠን ፈረድሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ። “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። የሚያስፈራቸው ማንም ሳይኖር በምድራቸው ያለ ሥጋት በሚኖሩበት ጊዜ፣ ውርደታቸውንና ለእኔ ባለ መታመን የኖሩበትን ዘመን ይረሳሉ። ከአሕዛብ ምድር መልሼ ሳመጣቸው፣ ከጠላቶቻቸው አገር ስሰበስባቸው የራሴን ቅድስና በእነርሱ በኩል በብዙ ሕዝቦች ፊት አሳያለሁ። በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ከእንግዲህ ፊቴን ከእነርሱ አልሰውርም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፈስሳለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
ሕዝቅኤል 39:21-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፥ ስለ በደሉኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ ሸሸግሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ። እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደርግሁባቸው፥ ፊቴንም ከእነርሱ ሸሸግሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ። እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም፥ ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፥ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 39:21-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ክብሬን በሕዝቦች መካከል እገልጣለሁ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ተግባራዊ ያደረግኹትን ፍርዴንና እነርሱን የቀጣሁበትን ኀይሌን ያያሉ። እስራኤላውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። እስራኤላውያን ተማርከው የሄዱትም እኔን በመበደላቸው ምክንያት መሆኑን ሕዝቦች ሁሉ ያውቃሉ፤ እኔ ችላ ስላልኳቸው ጠላቶቻቸው በጦርነት ድል አድርገው ሁላቸውንም ገድለዋቸዋል። እንደ ርኲሰታቸውና እንደ በደላቸው አደረግሁባቸው፤ ርዳታም አላደረግሁላቸውም።” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁን ግን የያዕቆብ ልጆች ለሆኑት ለእስራኤል ሕዝብ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ እንደገናም አበለጽጋቸዋለሁ፤ ቅዱስ ስሜም እንዳይሰደብ እከላከላለሁ። የሚያስፈራቸው ነገር ሳይኖር በገዛ ምድራቸው በሰላም ይኖሩ በነበረ ጊዜ የፈጸሙትን አሳፋሪ ተግባርና ለእኔ አለመታመናቸውን ሁሉ ይረሳሉ። እነርሱን ከሕዝቦች መካከል ስመልሳቸውና ከጠላቶቻቸው አገሮችም ብዙ ሕዝቦች እያዩ ስሰበስባቸው በእነርሱ አማካይነት ቅድስናዬን እገልጣለሁ። ተማርከው ወደ ስደት እንዲሄዱ ያደረግኋቸው እኔ ብሆንም እንኳ አሁን ከእነርሱ አንድም ሰው ወደኋላ ሳይቀር ወደ ገዛ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጌአለሁ። ስለዚህ ሕዝቤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ። መንፈሴን በእስራኤል ሕዝብ ላይ አፈሳለሁ፤ ዳግመኛም ችላ አልላቸውም፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
ሕዝቅኤል 39:21-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ክብሬን ለአሕዛብ እሰጣለሁ፥ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን እና በላያቸው ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። ከዚያች ቀን ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ። የእስራኤል ቤት በበደላቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ አሕዛብ ያውቃሉ፤ እኔን ስለ በደሉኝ፥ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። እንደ ርኩሰታቸውና እንደ መተላለፋቸው መጠን አደርግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው በሰላም በተቀመጡ ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ይሸከማሉ። ይህም የሚሆነው ከአሕዛብ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በእነሱ በተቀደስሁ ጊዜ ነው። እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ በአሕዛብ እንዲማረኩ አድርጌአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና፥ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አላስቀርም። ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሰውርም፥ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።