ሕዝቅኤል 37:4-10
ሕዝቅኤል 37:4-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእናንተ ላይ የሕይወትን መንፈስ አመጣለሁ። ጅማትንም እሰጣችኋለሁ፤ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ ቍርበትን እዘረጋለሁ፤ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፤ እነሆም መናወጥ ሆነ፤ አጥንቶችንም እየራሱ በሆነ በሰውነቱ ከአጥንቶች ጋር አንድ አደረጋቸው። እኔም አየሁ፤ እነሆም ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም ወጣ፤ ቍርበትም በላያቸው ተዘረጋ፤ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ! ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ እነዚህ ሙታን በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል” አለኝ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንፋሽም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
ሕዝቅኤል 37:4-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ! ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ። ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቈዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ” ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋራ ተጋጠመ። እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቈዳም ሸፍኗቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’ ” ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
ሕዝቅኤል 37:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ። ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
ሕዝቅኤል 37:4-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ብለህ ትንቢት ተናገር፦ እናንተ ደረቅ አጥንቶች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በውስጣችሁ እስትንፋስ በማስገባት እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። ጅማትና ሥጋ በመስጠት ቆዳ አለብሳችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አስገብቼ እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርኩ፤ መናገርም እንደ ጀመርኩ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ሰማሁ፤ አጥንቶቹም እርስ በርሳቸው እየተገጣጠሙ መያያዝ ጀመሩ። በመመልከት ላይ ሳለሁም አጥንቶቹ በጅማትና በሥጋ እንዲሁም በቈዳ ተሸፈኑ፤ እስትንፋስ ግን አልነበራቸውም። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ነፋስ ከአራቱም ማእዘን መጥቶ ሕይወት እንዲያገኙ በእነዚህ በድኖች ላይ እንዲነፍስ ንገረው።” እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርሁ፤ በእነርሱ ሁሉ ውስጥ እስትንፋስ ገባባቸው፤ ሁሉም ሕይወት አግኝተው ቆሙ፤ እጅግ ብዙ ሠራዊትም ሆኑ።
ሕዝቅኤል 37:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የጌታን ቃል ሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእናንተ ላይ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ። ጅማትንም አደርግላችኋለሁ፥ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ ቆዳ አለብሳችኋለሁ፥ በውስጣችሁ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢትንም ስናገር እነሆ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ነበር፥ አጥንት ከአጥንቱ ጋር እየሆነ አጥንቶች አንድ ላይ ሆኑ። እኔም አየሁ፥ እነሆ ጅማትና ሥጋ ነበረባቸው፥ ቆዳም ከላይ እስከ ታች ሸፈናቸው፥ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። እንዲህም አለኝ፦ “ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር የሰው ልጅ ሆይ፥ ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ በሕይወት እንዲኖሩ በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’” እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ እስትንፋስም በውስጣቸው ገባ፥ ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግ በጣም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።