ሕዝቅኤል 36:26-31
ሕዝቅኤል 36:26-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አዲስ ልብንም እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ በትእዛዜም እንድትሄዱ አደርጋችኋለሁ፤ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህልንም እጠራዋለሁ፤ አበዛውማለሁ፤ ራብንም አላመጣባችሁም። ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን መከር አበዛለሁ። ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፤ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
ሕዝቅኤል 36:26-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ። ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝቤም ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋሁ። ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም። ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ። ከዚያም ክፉ መንገዳችሁንና የረከሰ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁና ስለ አስጸያፊ ድርጊታችሁ ራሳችሁን ትጠላላችሁ።
ሕዝቅኤል 36:26-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፥ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፥ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም። ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ። ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
ሕዝቅኤል 36:26-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ ከሰውነታችሁ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን አሳድርባችኋለሁ፤ የሰጠኋችሁንም ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችሉ አደርጋችኋለሁ። ከዚያም በኋላ ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ እናንተ ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ። ከርኲሰታችሁ ነገር ሁሉ አድናችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራብ እንዳይደርስባችሁ እህል እንዲበዛላችሁ አዛለሁ። የዛፋችሁና የእርሻችሁ ፍሬ ሁሉ እንዲበዛ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን በአሕዛብ መካከል የሚያዋርድ ራብ አይደርስባችሁም። መጥፎ ጠባያችሁንና ትፈጽሙት የነበረውንም ክፉ ሥራ ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በኃጢአታችሁና ትፈጽሙት በነበረው የረከሰ ሥራ ምክንያት ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
ሕዝቅኤል 36:26-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋያማ ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ በትእዛዜ እንድትሄዱና ፍርዴን እንድትጠብቁ አደርጋችኋለሁ ትፈጽሟቸዋላችሁም። ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራዋለሁ አበዛዋለሁም፥ ረኃብም አላመጣባችሁም። የረኃብን ስድብ ዳግም ከመንግሥታት እንዳትቀበሉ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ምርት አበዛለሁ። ክፉዎች መንገዶቻችሁንና መልካም ያልሆኑ ሥራዎቻችሁን ታስባላችሁ፥ ስለ በደሎቻችሁና ስለ ርኩሰቶቻችሁም ራሳችሁን ትጠላላችሁ።