ሕዝቅኤል 36:25-36
ሕዝቅኤል 36:25-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ከርኵሰታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ፤ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ። አዲስ ልብንም እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ በትእዛዜም እንድትሄዱ አደርጋችኋለሁ፤ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህልንም እጠራዋለሁ፤ አበዛውማለሁ፤ ራብንም አላመጣባችሁም። ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን መከር አበዛለሁ። ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፤ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኀጢአታችሁ ሁሉ በአነጻኋችሁ ጊዜ በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ፤ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። ባድማ የነበረች፥ በመንገደኛም ሁሉ ዐይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች። ሰዎችም ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፤ የፈረሱት፥ ባድማ የሆኑት፥ የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል፤ ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ። በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ፥ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ፥ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።
ሕዝቅኤል 36:25-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኩሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ። አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ። ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝቤም ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋሁ። ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም። ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ። ከዚያም ክፉ መንገዳችሁንና የረከሰ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁና ስለ አስጸያፊ ድርጊታችሁ ራሳችሁን ትጠላላችሁ። ለእናንተ ስል ይህን እንደማላደርግ እንድታውቁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአድራጎታችሁ ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ! “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከኀጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን፣ ከተሞቻችሁ እንደ ገና መኖሪያ ይሆናሉ። የፈረሱትም እንደ ገና ይታደሳሉ። በዐላፊ አግዳሚው ዐይን ጠፍ ሆኖ ይታይ የነበረው ባድማ መሬት ይታረሳል። እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ። ከዚያም በዙሪያችሁ የነበሩ የቀሩት አሕዛብ ፈርሶ የነበረውን መልሼ የሠራሁ፣ ጠፍ የነበረውን ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ።’
ሕዝቅኤል 36:25-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፥ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፥ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም። ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ። ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ባነጻኋችሁበት ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። ባድማ የነበረች በመንገደኛም ሁሉ ዓይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች። ሰዎችም፦ ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፥ የፈረሱት ባድማ የሆኑት የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ። በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።
ሕዝቅኤል 36:25-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በእናንተ ላይ ንጹሕ ውሃ በመርጨት ከጣዖት አምልኮአችሁና ከርኲሰታችሁ ሁሉ እንድትነጹ አደርጋለሁ። አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ ከሰውነታችሁ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን አሳድርባችኋለሁ፤ የሰጠኋችሁንም ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችሉ አደርጋችኋለሁ። ከዚያም በኋላ ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ እናንተ ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ። ከርኲሰታችሁ ነገር ሁሉ አድናችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራብ እንዳይደርስባችሁ እህል እንዲበዛላችሁ አዛለሁ። የዛፋችሁና የእርሻችሁ ፍሬ ሁሉ እንዲበዛ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን በአሕዛብ መካከል የሚያዋርድ ራብ አይደርስባችሁም። መጥፎ ጠባያችሁንና ትፈጽሙት የነበረውንም ክፉ ሥራ ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በኃጢአታችሁና ትፈጽሙት በነበረው የረከሰ ሥራ ምክንያት ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። እኔ የማደርገውን ነገር ሁሉ ለእናንተ ብዬ የማላደርግ መሆኔ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ስለዚህ እስራኤል ሆይ! በአካሄዳችሁ ኀፍረትና ውርደት ይሰማችሁ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ጊዜ የፈራረሱትን ሁሉ በመገንባት እንደገና በከተሞቻችሁ እንድትኖሩ አደርጋለሁ። በእርሻዎቻችሁ በኩል በሚያልፉ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ባድማ ሆና ትቈጠር የነበረችው ምድር ትታረሳለች። ተመልካችም ሁሉ ‘ጭራሽ ምድረ በዳ ሆና የነበረች ይህች ምድር እንዴት የዔደንን ገነት መሰለች! ቀድሞ ባድማ ወናና የፍርስራሽ ክምር ሆነው የነበሩትስ ከተሞች እንዴት እንደገና ሕዝብ ሊኖርባቸውና የተመሸጉ ሊሆኑ ቻሉ?’ ይላሉ። በዚያን ጊዜ ከጥፋት የተረፉት የጐረቤት አገሮች ሕዝብ ሁሉ የፈረሱ ከተሞችን መልሼ የሠራሁና ባድማ የሆነውን ቦታ ያለመለምኩ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ እንደምፈጽም ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ።”
ሕዝቅኤል 36:25-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእናንተ ላይ ንጹሕ ውኃ እረጫለሁ እናንተም ትነጻላችሁ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ። አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋያማ ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ በትእዛዜ እንድትሄዱና ፍርዴን እንድትጠብቁ አደርጋችኋለሁ ትፈጽሟቸዋላችሁም። ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራዋለሁ አበዛዋለሁም፥ ረኃብም አላመጣባችሁም። የረኃብን ስድብ ዳግም ከመንግሥታት እንዳትቀበሉ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ምርት አበዛለሁ። ክፉዎች መንገዶቻችሁንና መልካም ያልሆኑ ሥራዎቻችሁን ታስባላችሁ፥ ስለ በደሎቻችሁና ስለ ርኩሰቶቻችሁም ራሳችሁን ትጠላላችሁ። ይህንን የሠራሁት ለእናንተ እንዳልሆና በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። በአላፊ አግዳሚው ሁሉ ዐይን ባድማ የነበረች፥ ባድማዋ ምድር ትታረሳለች። “ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆነች፤ የወደሙት፥ ባድማ የሆኑት፥ የፈረሱት ከተሞች አጥር ተሰርቶላቸዋል፥ መኖሪያም ሆነዋል” ይላሉ። በዙሪያችሁም የቀሩት መንግሥታት፥ የፈረሱትን ስፍራዎች የሠራሁ፥ ባድማ የሆነውንም የተከልሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።