ሕዝቅኤል 20:1-38
ሕዝቅኤል 20:1-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፥ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝ! አልመልስላችሁም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን በቀልን እበቀላቸዋለሁ፤ የሰው ልጅ ሆይ! የአባቶቻቸውን ኀጢአት አስታውቃቸው። እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት በመረጥሁበት፥ ለያዕቆብም ቤት ዘር በታወቅሁበት ቀን፥ በግብፅም ምድር በተገለጥሁላቸው ጊዜ እጄን አንሥቼ፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። በዚያ ቀን ከግብፅ ምድር ወዳዘጋጀሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ ከምድር ሁሉ ወደምትበልጥ ምድር አወጣቸው ዘንድ እጄን አነሣሁ። እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ ርኵሰቱን ከፊቱ ያስወግድ፤ በግብፅም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። እነርሱ ግን ዐመፁብኝ፤ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ርኵሰቱን ከፊቱ አላስወገደም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ በግብፅ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በመካከላቸው በአሉ፥ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። “ከግብፅም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። ሰው ቢያደርገው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴንም ሰጠኋቸው፤ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። ነገር ግን የእስራኤልን ቤት በምድረ በዳ በትእዛዜ ሂዱ አልኋቸው፤ አልሄዱምም፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ሕጌን አፈረሱ፤ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ከሁሉ በላይ የሚሆን ስሜን እንዳያረክሱ አደረግሁ። ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ከምድር ሁሉ ወደምታምር ወደ ሰጠኋቸው ምድር እንዳላገባቸው በምድረ በዳ በእነርሱ ላይ ፈጽሜ እጄን አነሣሁ። ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዐቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና በልባቸው ዐሳብ ሄዱ። ነገር ግን እኔ እንደ አላጠፋቸው፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ እንደ አልጨርሳቸው ዐይኔ ራራችላቸው። “ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ልማድ አትሂዱ፤ ሥርዐታቸውንም አትጠብቁ፤ በበደላቸውም አንድ አትሁኑ፤ አትርከሱም። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጓትም። ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሁኑ። ልጆቻቸው ግን አማረሩኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጉትም፤ በሥርዐቴም አልሄዱም፤ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ከሁሉ የሚበልጠው ስሜ እንዳይረክስ አደረግሁ። ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በሀገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ በእነርሱ ላይ እጄን አነሣሁ። ፍርዴን አላደረጉምና፥ ሥርዐቴንም ጥሰዋልና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፥ ዐይኖቻቸውም የአባቶቻቸውን ዐሳብ ተከትለዋልና። ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዐት፥ በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በአመጡልኝ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ በአደረጉት ዐመፅ አስቈጡኝ። እሰጣቸውም ዘንድ እጄን ወደ አነሣሁላቸው ምድር አገባኋቸው፤ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ፥ ቅጠላማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፤ በዚያም ለጣዖቶቻቸው መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ በዚያም የሚያስቈጣኝን፤ ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ፤ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ። እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድን ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ በአባቶቻችሁ ኀጢአት ረከሳችሁ፤ አመነዘራችሁ፤ ርኵሰታቸውንም ተከተላችሁ። ቍርባናችሁን በአቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በዐሳባችሁ ሁሉ ረከሳችሁ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! እኔስ እመልስላችኋለሁን? እኔ ሕያው ነኝ! አልመልስላችሁም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፤ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ ዐሳብ አይፈጸምላችሁም። “እኔ ሕያው ነኝ! በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባትም ሀገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትሬም በታች አሳልፋችኋለሁ፤ በቍጥርም እወስዳችኋለሁ። ከእናንተም ዘንድ ዐመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ፤ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 20:1-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሰባተኛው ዓመት፣ በዐምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ። ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጥላቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብጽም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው።” በዚያ ቀን፣ ከግብጽ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው። እኔም፣ “እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” አልኋቸው። “ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብጽ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር። ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብጽ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ። ስለዚህ ከግብጽ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው። ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው። ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው። “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር። ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ። ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤ ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋራ ተጣብቋልና። እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም። ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ። በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ።” “ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር። ነገር ግን ከግብጽ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ። ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤ ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋራ ተጣብቋል። እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’ “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ ታማኝነታቸውን በማጕደላቸው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ። እኔም፣ የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?’ ” አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ይጠራል። “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን? ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም። በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ። ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋራ እፋረዳለሁ። በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋራ እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋራ እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋራ አጣብቃችኋለሁ። በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 20:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝና በእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ በውኑ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኵሰት አስታውቃቸው። እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ለያዕቆብም ቤት ዘር በማልሁበት ቀን በግብጽም ምድር በተገለጥሁላቸውና፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ብዬ በማልሁላችሁ ጊዜ፥ በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላችሁ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው፥ እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፥ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፥ በዚህም ጊዜ፦ በግብጽ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፥ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም። ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፥ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። ሰንበታቴንም ቀድሱ፥ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፥ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለህ አልሁ። ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፥ ፍርዴን አላደረጉምና፥ ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፥ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመፅ አስቈጡኝ። እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቈጣኝን ቍርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ። እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኵሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? ቍርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም። እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፥ ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 20:1-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በተሰደድን በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ጥቂቶቹ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊጠይቁኝ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ለእነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፥ ‘ፈቃዴን ለማወቅ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው እንደ መሆኔ ምንም ነገር እንድትጠይቁኝ አልፈቅድላችሁም፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ “የሰው ልጅ ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ ትፈርድባቸዋለህን? ትፈርድባቸዋለህን? እንግዲያውስ አባቶቻቸው ያደረጉትን አጸያፊ ነገር እንዲያውቁ አድርጋቸው። እንዲህም በላቸው፦ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን በመረጥኩ ጊዜ ለያዕቆብ ዘር በግብጽ ምድር ራሴን በማሳወቅ ቃል ገባሁላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኳቸው። ከግብጽ ምድር አወጣኋቸው፤ ለእነርሱ የመረጥኩላቸው ምድር በማርና በወተት የበለጸገች ነበረች፤ እርስዋም ከዓለም ምድር ሁሉ ይበልጥ የተዋበች ነበረች፤ ወደዚያች ምድርም እንደማስገባቸው ቃል የገባሁላቸው በዚያን ጊዜ ነው። እንዲህም አልኳቸው፦ ‘እያንዳንዳችሁ የምታተኲሩባቸውን አጸያፊ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖቶችም ራሳችሁን አታርክሱ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።’ ነገር ግን እነርሱ ዐመፀኞች ሆኑ እንጂ እኔን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ዐይኖቻቸው ያተኰሩባቸውን አጸያፊ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖት ማምለክ አልተዉም፤ ስለዚህ በግብጽ በነበሩበት ጊዜ ቊጣዬን ላወርድባቸው አስቤ ነበር። ነገር ግን አብረዋቸው በሚኖሩት ሕዝቦች ፊት ከግብጽ እንደማወጣቸው ለእስራኤላውያን ቃል ገብቼ ነበር፤ ስለዚህ ስሜ እንዳይነቀፍ እነርሱን ከግብጽ እንዲወጡ አድርጌአለሁ። “ስለዚህም ከግብጽ መርቼ ወደ በረሓ አመጣኋቸው፤ ለሚታዘዘው ሁሉ በሕይወት መኖር የሚችልበትን ሕጌን ሰጠኋቸው፤ ሥርዓቴንም አስተማርኳቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ መሆኔን ያውቁ ዘንድ ሰንበትን ማክበራቸው በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት እንዲሆን አደረግሁ። ነገር ግን እስራኤላውያን በበረሓ ሳሉ እንኳ በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚያስገኝለትን ሕጌንና ሥርዓቴን ጣሱ፤ ፈጽመውም ሰንበትን አረከሱ፤ በዚያም በበረሓ ቊጣዬን በእነርሱ ላይ በመግለጥ ላጠፋቸው አስቤ ነበር፤ ነገር ግን እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር መርቼ ሳወጣ በተመለከቱኝ ሕዝቦች ፊት ስሜ እንዳይነቀፍ ይህን ሁሉ አላደረግሁም። ከዚህም በላይ ከዓለም ምድር ሁሉ ውብ የሆነችውንና በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እሰጣችኋለሁ ብዬ ቃል ገብቼላቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በበረሓ እያሉ ወደዚያ እንደማላስገባቸው አረጋግጬ ነገርኳቸው። ይህንንም ውሳኔ ያደረግኹበት ምክንያት ልባቸው ወደ ጣዖቶቻቸው በማምራት ሕጌንና ሥርዓቴን ስላፈረሱ፥ ሰንበትንም ስላረከሱ ነው።” ይህም ሆኖ ስለ ራራሁላቸው አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልጨረስኳቸውም። ለልጆቻቸውም እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፦ “የቀድሞ አባቶቻችሁ ባወጡት ድንጋጌ አትመሩ፤ ሥርዓታቸውንም አትከተሉ፤ ወይም በጣዖቶቻቸው አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ ለሕጌም በጥንቃቄ ታዘዙ። እኔ ከእናንተ ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን ምልክት ይሆንላችሁ ዘንድ፥ እንዲሁም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ያስታውሳችሁ ዘንድ ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርጉት። “ነገር ግን ልጆቻቸው በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ለሚፈጽመው ሁሉ ሕይወት የሚያስገኝለትን ሕጌን አፈረሱ፤ ሕጎቼንም አልጠበቁም፤ ሰንበትንም አረከሱ፤ በዚያም በበረሓ ሳሉ የቊጣዬን ኀይል በእነርሱ ላይ በማውረድ ሁሉንም ላጠፋቸው አስቤ ነበር። ነገር ግን እስራኤላውያንን ከግብጽ ማውጣቴን በተመለከቱ ሕዝቦች ዘንድ ስሜ እንዳይነቀፍ ይህን አላደረግሁም። ከዚህም በላይ በተለያዩ አገሮች በሕዝቦች መካከል እንደምበታትናቸው በምድረ በዳ እያሉ በመሐላ አረጋግጬ ነገርኳቸው። ይህንንም ያደረግኹት ሕጌን ስለ ተላለፉ፥ ሥርዓቴንም ስላልተከተሉ፥ ሰንበትን ስላረከሱ፥ የቀድሞ አባቶቻቸውንም ጣዖቶች ስለ አመለኩ ነው። “ከዚህ በኋላ መልካም ያልሆነውን ሕግና ሊኖሩበት ያልቻሉትን ሥርዓት ሰጠኋቸው። የበኲር ልጆቻቸውን እስከ መሠዋት ድረስ ተቀባይነት የሌለውን መሥዋዕት በማቅረብ ራሳቸውን እንዲያረክሱ ተውኳቸው፤ ይህንንም ያደረግኹት እነርሱን መቀጣጫ የማደርጋቸው እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቁ ዘንድ ነው። “እንግዲህ የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ አባቶቻቸው እኔን በመካድ በዚህ ተዳፈሩኝ። ለእነርሱ እንደምሰጣቸው ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር አመጣኋቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱ ከፍተኛ ኰረብቶችንና ለምለም ዛፎችን ባዩ ጊዜ በሁሉም ላይ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በሚቃጠል መሥዋዕታቸው፥ መዓዛው በሚጣፍጥ ዕጣናቸውና ለመሥዋዕትም በሚያፈሱት የመጠጥ ቊርባናቸው አስቈጡኝ፤ እኔም ‘እነዚህ የምትሄዱባቸው ከፍተኛ ቦታዎች ምንድን ናቸው?’ ብዬ ጠየቅኋቸው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ‘ከፍተኛ ቦታዎች’ ተብለው ይጠራሉ። አሁንም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንደ አባቶቻችሁ ራሳችሁን በማርከስና የእነርሱን አጸያፊ ጣዖቶች በማምለክ ለምን ትስታላችሁ? ዛሬም እንኳ ተመሳሳይ መባ ታቀርባላችሁ፤ ልጆቻችሁን በእሳት ውስጥ መሥዋዕት አድርጋችሁ በማቅረብ በእነዚያው በጥንታውያኑ ጣዖቶች ራሳችሁን ታረክሳላችሁ፤ ይህን ሁሉ ካደረጋችሁ በኋላ እናንተ እስራኤላውያን ፈቃዴ ምን እንደ ሆነ ለመጠየቅ ትመጣላችሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር በእርግጥ ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ ምንም ነገር እንድትጠይቁኝ አልፈቅድላችሁም! እንደ ሌሎች ሕዝቦች ወይም ለዛፍና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ በሌሎች አገሮች እንደሚኖሩ አሕዛብ ለመሆን ወስናችኋል፤ ነገር ግን ይህ ከቶ ሊሆን አይችልም።’ ” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ በእርግጥ በሥልጣኔ፥ በሙሉ ኀይሌና በቊጣዬ በእናንተ ላይ እነግሣለሁ። ከተበታተናችሁባቸው አገሮችና ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ የምሰበስባችሁም በኀይሌና ሥልጣኔ፥ በማወርደው ቊጣዬ ነው። ‘የሕዝቦች በረሓ’ ተብላ ወደምትጠራ ምድር አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ዐይናችሁ እያየ እፈርድባችኋለሁ፤ በግብጽ በረሓ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ፈረድኩ በእናንተም ላይ እፈርዳለሁ፤” ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። “ከሥልጣኔ ሥር አደርጋችኋለሁ፤ ወደ ቃል ኪዳኔ ግዴታም አመጣችኋለሁ። ዐመፀኞችንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ አሁን ከሚኖሩባቸው አገሮች አወጣቸዋለሁ፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ምድር እንዲመለሱ ከቶ አልፈቅድላቸውም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
ሕዝቅኤል 20:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች ጌታን ሊጠይቁ መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ እኔን ልትጠይቁ መጣችሁን? እኔ ሕያው ነኝ፥ ለእናንተ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኩሰት አስታውቃቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፥ ለያዕቆብ ቤት ዘር ማልሁላቸው፥ በግብጽም ምድር ራሴን ገለጥሁላቸው፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ ብዬ ማልሁላቸው። በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላችሁ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው። እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ፦ በግብጽ ምድር መካከል ቁጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። የምቀድሳቸውም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቁጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፥ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም። ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቁጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤ ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። እኔም ጌታ እንደሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመጽ አስቆጡኝ። እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ። እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኩሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም። እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤ ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።