ዘፀአት 36:1-5
ዘፀአት 36:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ባስልኤልና ኤልያብ፥ ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው በልባቸውም ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ።” ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም ዕውቀትንና ጥበብን በልቡናቸው ያሳደረባቸውንና ጥበብ ያላቸውን፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ሥራውን ሠርተው ይፈጽሙ ዘንድ ጠራቸው። እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። እያንዳንዳቸው በሚሠሩት የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ መጡ፤ እነርሱም ለሙሴ፥ “እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ሥራ ከሚበቃ በላይ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ” ብለው ነገሩት።
ዘፀአት 36:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ሁሉ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ጥበብንና ችሎታን የሰጣቸው፣ ባስልኤል፣ ኤልያብና ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ሥራውን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ይሥሩት።” ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) ችሎታ የሰጣቸውን፣ መጥተው ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ጥበብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ አስጠራ። የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ። ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤ ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።
ዘፀአት 36:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኞችም ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ። ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው። እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። የመቅደሱንም ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ የሚያደርጉትን ሥራ ትተው መጡ፥ እነርሱም ሙሴን፦ እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ ብለው ተናገሩት።
ዘፀአት 36:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ባጽልኤልና ኦሆሊአብ እንዲሁም ለተቀደሰው ድንኳን ዝግጅት እግዚአብሔር ማናቸውንም ሥራ ለመሥራት ችሎታንና ዕውቀትን የሰጣቸው ሌሎች ሰዎች እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ይሠራሉ።” ሙሴም ባጽልኤልንና ኦሆሊአብን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልዩ ችሎታ የሰጣቸውንና ለመርዳት ፈቃደኞች የነበሩትን ሌሎችን ጥበበኞች ሁሉ ጠርቶ ሥራውን እንዲጀምሩ ነገራቸው። እነርሱም እስራኤላውያን ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ እንዲውል ያመጡትን ስጦታ ከሙሴ እጅ ተቀበሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን በየማለዳው ስጦታቸውን ለሙሴ ከማምጣት አልተቈጠቡም። ከዚህም በኋላ ሥራውን የሚያከናውኑት ጥበበኞች ሁሉ ሥራቸውን ትተው ወደ ሙሴ በመሄድ፥ “ሕዝቡ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ እጅግ ብዙ ስጦታ በማምጣት ላይ ናቸው” አሉት።
ዘፀአት 36:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ባስልኤል፥ ኤልያብና ጥበበኞች ሁሉ፥ የመቅደሱን አገልግሎት ሥራ ሁሉ እንዲያደርጉና እንዲያውቁ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ። ሙሴም ባስልኤልን፥ ኤልያብንና ጌታ በልቡ ጥበብን ያሳደረበትን ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውን ለመሥራት ልቡ ያነሣሣውን ሁሉ ጠራቸው። የመቅደሱን ሥራ ለመሥራት የእስራኤል ልጆች ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ወሰዱ። እነዚያም በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ስጦታ አሁንም ማለዳ ማለዳ ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፥ ሙሴንም፦ “ሕዝቡ ጌታ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ አመጡ” አሉት።