ዘፀአት 34:5-8
ዘፀአት 34:5-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። ጌታም በፊቱ አለፈ፥ “ስሜም ጌታ እግዚአብሔር፥ መሓሪ፥ ይቅር ባይ፥ ከመዓት የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ ለብዙ ሺህ ጽድቅን የሚጠብቅ፥ ቸርነትን የሚያደርግ፥ አበሳንና መተላለፍን፥ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኀጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” ሲል አወጀ። ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጎነበሰና ለእግዚአብሔር ሰገደ፦
ዘፀአት 34:5-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ። እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።” ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤
ዘፀአት 34:5-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ፦ እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ፦
ዘፀአት 34:5-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ከእርሱ ጋር በዚያ ቆመ፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ቅዱስ ስሙንም አስታወቀው። እግዚአብሔር በፊቱ ሲያልፍ እንዲህ ብሎ ዐወጀ፤ “እኔ እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነኝ፤ እኔ ለቊጣ የዘገየሁ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬና ታማኝነቴ የበዛ ነው፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬንም እስከ ብዙ ሺህ ትውልድ እጠብቃለሁ፤ በደልን መተላለፍንና ኃጢአትን ሁሉ ይቅር እላለሁ፤ ነገር ግን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ ስለ ወላጆቻቸው ኃጢአት ከመቅጣት አልገታም።” ሙሴም ወዲያውኑ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤
ዘፀአት 34:5-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም በደመና ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የጌታንም ስም አወጀ። ጌታም በፊቱ አልፎ እንዲህ ብሎ አወጀ፦ “ጌታ፥ ጌታ፥ መሓሪ አምላክ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽ፥ ፅኑ ፍቅሩና እውነቱ የበዛ፥ ፅኑ ፍቅሩን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በደለኛውን ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆችና በልጅ ልጆች ላይ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ የሚያመጣ አምላክ ነው።” ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተደፍቶ ሰገደ፦