ዘፀአት 34:29-33
ዘፀአት 34:29-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ ጽላት በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እነሆ፥ ፊቱ እንዳንጸባረቀ ሙሴን በአዩ ጊዜ፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ።
ዘፀአት 34:29-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር። አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር። ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው። ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው። ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ።
ዘፀአት 34:29-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። አሮንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩን አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ።
ዘፀአት 34:29-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቈይቶ ስለ ነበር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባቸውን ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ፊቱ አበራ፤ ለእርሱ ግን ይህ ሁሉ አይታወቀውም ነበር። አሮንና ሕዝቡ ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ ፊቱ እንደሚያበራ ተመልክተው ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። ሙሴ ግን ጠራቸው፤ አሮንና የሕዝቡ አለቆች ወደ እርሱ ቀርበው አነጋገራቸው። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ እርሱ መጡ፤ ሙሴም በሲና ተራራ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሕግ ሁሉ ሰጣቸው። ሙሴ ከእነርሱ ጋር መነጋገሩን ካበቃ በኋላ ፊቱን በሻሽ ሸፈነ፤
ዘፀአት 34:29-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴ ከሲና ተራራ በሚወርድበት ጊዜ እንዲህ ሆነ፥ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች ከተራራው በሚወርድበት ጊዜ በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተነጋገረ ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። አሮንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ ፊቱ ያንጸባርቅ ነበር፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። ሙሴ ግን ጠራቸው፥ አሮንና የማኅበሩ አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም አነጋገራቸው። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ጌታ በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ።