ዘፀአት 32:30-35
ዘፀአት 32:30-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ፥ “እናንተ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ አሁንም አስተሰርይላችሁ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤” አላቸው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁንም ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደሆነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በፊቴ የበደለውን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁንም ሂድ፤ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ቦታ ምራ፤ እነሆ፥ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኀጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ” አለው። አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።
ዘፀአት 32:30-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው። ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ። አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።” እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርሁት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።” አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።
ዘፀአት 32:30-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ፦ እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፦ ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምግአበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው። አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።
ዘፀአት 32:30-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱም ሙሴ ለእስራኤላውያን “አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ ነገር ግን እነሆ አሁንም እንደገና እግዚአብሔር ወደሚገለጥበት ተራራ እወጣለሁ፤ ምናልባት ስለ ኃጢአታችሁ ይቅርታ አስገኝላችሁ ይሆናል” አለ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል በፊትህ ፈጽሞአል፤ ከወርቅ የሠሩትን ምስል አምላክ አድርገው ሰግደውለታል፤ እባክህ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ይቅር የማትላቸው ከሆነ ግን የሕዝብህ ስሞች ከተጻፉበት መዝገብ የእኔን ስም ደምስስ።” እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ስሞቻቸውን ከመዝገቤ የምደመስሰው ኃጢአት በመሥራታቸው ያሳዘኑኝን ሰዎች ነው። አሁንም ሂድ፤ ወደነገርኩህ ስፍራ ሕዝቡን ምራ፤ መልአኬም እየመራህ በፊትህ እንደሚሄድ አስታውስ፤ ነገር ግን ይህን ሕዝብ ስለ ኃጢአቱ የምቀጣበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።” የወርቅ ጥጃ ምስል እንዲሠራላቸው አሮንን በማስገደዳቸው እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ከባድ በሽታ ላከ።
ዘፀአት 32:30-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በማግስቱም ሙሴ ለሕዝቡ “እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ ጌታ እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ ይሆናል” አላቸው። ሙሴም ወደ ጌታ ተመልሶ “ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁንም ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፥ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” አለ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። አሁንም ሂድ፥ ይህንንም ሕዝብ ወደ ነገርኩህ ስፍራ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን በላያቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ።” አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ ጌታ ሕዝቡን ቀሠፈ።