ዘፀአት 32:11-14
ዘፀአት 32:11-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አለም፥ “አቤቱ፥ በታላቅ ኀይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር በአወጣኸው በሕዝብህ ላይ ለምን ተቈጣህ? ግብፃውያንስ፦ ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው’ ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፤ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፤ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸው ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ዐስብ።” እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ይቅር አለ።
ዘፀአት 32:11-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነድዳል? ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው፣ ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።” ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።
ዘፀአት 32:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም፦ አቤቱ፥ ቁጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? ግብፃውያንስ፦ በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለህ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም፥ አስብ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።
ዘፀአት 32:11-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴ ግን እግዚአብሔር አምላኩን በመማለድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በሥልጣንህና በታላቅ ኀይልህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን ሕዝብህን እስከዚህ የምትቈጣው ስለምነው? ግብጻውያን ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣቸው ለክፉ ነገር፥ ማለት በተራራዎች ላይ ሊገድላቸውና ፈጽሞ ሊያጠፋቸው ነው’ እያሉ መዘባበቻ እንዲያደርጉን ለምን ትፈቅዳለህ? አሁንም ከቊጣህ ወደ ምሕረት ተመለስ፤ ይህንንም ሁሉ ጥፋት በሕዝብህ ላይ አታምጣ። አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ ዘራቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት ልታበዛውና የተስፋይቱንም ምድር ርስት ለዘለዓለም አድርገህ ልትሰጣቸው በመሐላ የገባህላቸውንም ቃል ኪዳን አስብ።” ስለዚህ እግዚአብሔር ከቊጣ ወደ ምሕረት ተመልሶ፥ ሊያመጣባቸው የነበረውን መቅሠፍት እንዲገታ አደረገ።
ዘፀአት 32:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም በጌታ አምላኩ ፊት ለመነ፥ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብጽ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ቁጣህ ስለምን ነደደ? ግብፃውያን ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከገጸ ምድር ሊያጠፋቸው ለክፋት ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከቁጣህ መዓት ተመለስ፥ በሕዝብህ ጥፋት ላይ ራራ። ‘ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም ምድር ሁሉ እንደተናገርሁት ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል’ ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባርያዎችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና እስራኤልን አስብ።” ጌታም በሕዝቡ ላይ አደርጋለሁ ያለውን ክፋ ነገር መለሰ።