ዘፀአት 32:1-10
ዘፀአት 32:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፥ “ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት። አሮንም፥ “በሚስቶቻችሁና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ጌጦች አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ በጆሮዎቻቸው ያሉትን የወርቅ ጌጦች ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፤ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም፥ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው። አሮንም በአየው ጊዜ መሠዊያውን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፥ “ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው” ሲል አወጀ። አሮንም በነጋው ማልዶ ተነሣ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ሠዋ፤ የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረበ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፥ “ከግብፅ ምድር ያወጣኻቸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ፤ ፈጥነህ ውረድ። ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፤ ሰገዱለትም፤ ሠዉለትም፤ ‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ። አሁንም ተቈጥቼ አጠፋቸው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
ዘፀአት 32:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይ ወርድ ብዙ እንደ ቈየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት። አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው። ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ። እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ። አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ። በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ” አለው። “ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ ዐንገተ ደንዳናዎችም ናቸው። አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
ዘፀአት 32:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፦ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። አሮንም፦ በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም፦ እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው። አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፦ ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ። በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ። ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠውለትም፦ እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
ዘፀአት 32:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እዚያ ብዙ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ በአንድነት በመሰብሰብ አሮንን ከበው “ያ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ በፊት በፊታችን እየሄዱ የሚመሩን አማልክትን ሥራልን” አሉት። አሮንም “ሚስቶቻችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ የሚያጌጡበትን የጆሮ ወርቅ ሁሉ ሰብስባችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ያላቸውን የወርቅ ጒትቻ ሁሉ አውልቀው ወደ አሮን አመጡለት። እርሱም የወርቅ ጒትቻውን ሁሉ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ የቀለጠውንም ወርቅ በቅርጽ መሥሪያ ውስጥ አግብቶ የወርቅ ጥጃ አድርጎ ሠራው። እነርሱም “እስራኤል ሆይ! ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ነው!” አሉ። አሮንም ይህን ባየ ጊዜ በወርቁ ጥጃ ፊት መሠዊያ ሠርቶ “ነገ ለእግዚአብሔር ክብር በዓል ይደረጋል” ሲል አስታወቀ። በማግስቱ ሰዎቹ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ እነርሱም ተቀምጠው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ከመጠን በላይ ሊፈነጥዙ ተነሡ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ ራሱን ስላረከሰ ፈጥነህ ውረድ፤ እነርሱ እንዲከተሉት ካዘዝኳቸው መንገድ ወዲያውኑ ወጥተዋል፤ ከቀለጠ ወርቅ ጥጃ ሠርተውም ሰግደውለታል፤ መሥዋዕትም አቅርበውለት ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን አምላካችን ይህ ነው’ ብለዋል። እነርሱ ምን ያኽል ልበ ደንዳኖች እንደ ሆኑ እኔ ዐውቃለሁ፤ አሁንም እነሆ፥ በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጥቼ ላጠፋቸው ስለ ተዘጋጀሁ ተወኝ፤ አንተንም ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
ዘፀአት 32:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፦ “ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ ተነሥና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት። አሮንም፦ “በሚስቶቻችሁ፥ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡ ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸው ተቀብሎ በቅርጽ መሥሪያ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃ አደረገው፤ እርሱም፦ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው። አሮንም አየውና መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፦ “ነገ የጌታ በዓል ነው” ሲል አወጀ። በማግስቱ ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የሰላም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ ውረድ፤ ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ለራሳቸውም ቀልጦ የተሠራ ጥጃ ሠሩ፥ ሰገዱለት፥ ሠዉለትም፦ ‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። አሁንም ቁጣዬ በእነርሱ ላይ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከአንተም ታላቅ ሕዝብ አደርጋለሁ።”