ዘፀአት 18:14-19
ዘፀአት 18:14-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮቶርም ሙሴ በሕዝቡ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቶ እንዲህ አለው፥ “ብቻህን ተቀምጠህ በሕዝቡ የምታደርገው ይህ ምንድን ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመዋል።” ሙሴም አማቱን፥ “ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ፍርድ ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፤ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ” አለው። የሙሴም አማት አለው፥ “አንተ የምታደርገው ይህ ነገር ትክክል አይደለም። አንተ፥ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ ይህ ነገር ይከብድብሃል፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሃለሁና ስማኝ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፤ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤
ዘፀአት 18:14-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዐማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ። ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጕዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።” የሙሴ ዐማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም። አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም። ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን የምትወክል መሆን አለብህ፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ።
ዘፀአት 18:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው። ሙሴም አማቱን፦ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። የሙሴም አማት አለው፦ አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤
ዘፀአት 18:14-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሙሴ ዐማት የትሮም ለሕዝቡ ያደርገው የነበረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ሁሉ ለሕዝቡ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? ሕዝቡ አንተን ለማነጋገር በመፈለግ ከጠዋት እስከ ማታ በዙሪያህ በመቆም እንደዚህ የሚያጨናንቅህና አንተም ይህን ሁሉ ጉዳይ በዳኝነት ለማየት ብቻህን የምትቀመጠው ለምንድነው?” ሙሴም ለዐማቱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ወደ እኔ ስለሚመጣ ነው፤ ሁለት ሰዎች ተጣልተውም ወደ እኔ ቢመጡ የትኛው ወገን ትክክል እንደሆን ለማሳወቅ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት እነግራቸዋለሁ።” ከዚህም በኋላ የትሮ እንዲህ አለ፦ “ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም፤ አንተን ራስህንም ሆነ ሕዝቡን በከንቱ ታደክማለህ፤ ብቻህን ሆነህ ይህን ሁሉ ለመሥራት ይከብድብሃል፤ እነሆ፥ እኔ አንድ ነገር ልምከርህ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ ሕዝቡን ወክለህ በእግዚአብሔር ፊት ጉዳያቸውን አቅርብ፤
ዘፀአት 18:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሙሴ አማትም ለሕዝቡ ያደርግ የነበረውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ “ለሕዝቡ የምታደርገው ይሄ ነገር ምንድነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመዋል፥ አንተ ብቻህን ለምን ተቀምጠሃል?” አለው። ሙሴም አማቱን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በአንድ ሰውና በጎረቤቱ መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ።” የሙሴ አማትም አለው፦ “እያደረግህ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ ይህ ነገር ይከብድሃልና፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን አቅርብ፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አቅርብ፤