ዘፀአት 15:22-25
ዘፀአት 15:22-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ። ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው።
ዘፀአት 15:22-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከቀይ ባሕር አሳልፎ ወደ ሱር በረሓ መራቸው፤ ሦስት ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዙ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ አላገኙም። ከዚህ በኋላ ማራ ወደ ተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበረ ሊጠጡት አልቻሉም፤ ማራ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት ይኸው ነበር። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጒረምረም “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሙሴም በብርቱ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አንድ እንጨት አሳየው፤ እርሱንም ወስዶ በውሃው ላይ በጣለው ጊዜ፥ ውሃው ወደጣፋጭነት ተለወጠ። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበት ደንብና ሥርዓት ሰጣቸው፤ በዚያም ፈተናቸው።
ዘፀአት 15:22-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራ ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፥ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ዕንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው።
ዘፀአት 15:22-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤
ዘፀአት 15:22-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም እስራኤልን ከቀይ ባሕር መራ፥ ወደ ሹር ምድረ በዳም ሄዱ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም መጡ፥ የማራንም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም መራራ ነበረና፤ ስለዚህ አንድ ሰው ማራ ብሎ ጠራው። ሕዝቡም፦ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እርሱም ወደ ጌታ ጮኸ፤ ጌታም ዛፍ አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፋጭ ሆነ። ጌታም በዚያ ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤