የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 1:6-14

ዘፀአት 1:6-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዮሴ​ፍም ሞተ፤ ወን​ድ​ሞ​ቹም፥ ያም ትው​ልድ ሁሉ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በዙ፤ ተባ​ዙም፤ የተ​ጠ​ሉም ሆኑ። እጅ​ግም ጸኑ፤ ምድ​ሪ​ቱም በእ​ነ​ርሱ ሞላች። በግ​ብፅ ዮሴ​ፍን ያላ​ወቀ ሌላ ንጉሥ ተነሣ። እር​ሱም ሕዝ​ቡን፥ “እነሆ፥ የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ሕዝብ ታላ​ቅና ብዙ ሆነ​ዋል፤ ከእ​ኛም ይልቅ በር​ት​ተ​ዋል፤ ኑ፤ እን​ጠ​በ​ብ​ባ​ቸው፤ የበዙ እን​ደ​ሆነ ጦር​ነት በመ​ጣ​ብን ጊዜ በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን ላይ ተደ​ር​በው በኋ​ላ​ችን ይወ​ጉ​ና​ልና፥ ከም​ድ​ራ​ች​ንም ያስ​ወ​ጡ​ና​ልና።” በብ​ርቱ ሥራም ያስ​ጨ​ን​ቋ​ቸው ዘንድ የሠ​ራ​ተ​ኞች አለ​ቆ​ችን ሾመ​ባ​ቸው፤ ለፈ​ር​ዖ​ንም ፌቶ​ምን፥ ራም​ሴ​ንና የፀ​ሐይ ከተማ የም​ት​ባል ዖንን ጽኑ ከተ​ሞች አድ​ር​ገው ሠሩ። ነገር ግን እን​ዳ​ስ​ጨ​ነ​ቁ​አ​ቸው መጠን እን​ዲሁ በዙ፤ እጅ​ግም ጸኑ ፤ ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች ይጸ​የ​ፉ​አ​ቸው ነበር። ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች በግ​ፍዕ ገዙ​አ​ቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡ​ብም፥ በእ​ር​ሻም ሥራ ሁሉ፥ በመ​ከ​ራም በሚ​ያ​ሠ​ሩ​አ​ቸው ሥራ ሁሉ፤ ሕይ​ወ​ታ​ቸ​ውን ያስ​መ​ር​ሩ​አ​ቸው ነበር።

ዘፀአት 1:6-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከጊዜ በኋላ ዮሴፍና ወንድሞቹ ያም ትውልድ በሙሉ ሞቱ፤ ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እየተዋለዱ በዙ፤ ቍጥራቸው እጅግ ከመጨመሩም የተነሣ የግብፅን ምድር ሞሏት። በግብፅም፣ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ነገሠ። እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤ ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋር አብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኰብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።” ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት። ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር። ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብፃውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።

ዘፀአት 1:6-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዘመናት ውስጥ ዮሴፍ፥ ወንድሞቹና የዚያ ትውልድ አባቶች ሁሉ ሞቱ። ሆኖም የእነርሱ ዘሮች የሆኑ እስራኤላውያን ተዋልደው ቊጥራቸው ከመብዛቱ የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሉአት፤ እጅግም ብርቱዎች ሆኑ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ዮሴፍ ያደረገውን ነገር የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። እርሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ እነዚህ እስራኤላውያን ቊጥራቸው በዝቶአል፤ የኀይላቸውም ብርታት አስጊ ሆኖብናል፤ ከዚህም የተነሣ ከጠላቶቻችን ጋር ተባብረው ከወጉን በኋላ ከአገሪቱ አምልጠው መሄድ ይችላሉ፤ ስለዚህ ቊጥራቸው እየበዛ እንዳይሄድ ኑ፤ አንድ ዘዴ እንፈልግ።” ከዚህ በኋላ በብርቱ ሥራ ይጨቊኑአቸው ዘንድ ጨካኞች የሆኑ አሠሪዎችን ሾሙባቸው፤ በዚህም ሁኔታ ዕቃ ማከማቻ የሆኑትን ፊቶምና ራምሴ የተባሉትን ከተሞች ለፈርዖን ሠሩ። ነገር ግን እስራኤላውያን በተጨቈኑ መጠን ቊጥራቸው ይበልጥ እየበዛና በምድሪቱም ላይ እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። ርኅራኄ በጐደለውም ጭካኔ በባርነት አሠሩአቸው። ጭቃ በማቡካት፥ ጡብ በማዘጋጀትና በእርሻ ውስጥ በጭካኔ ከባድ ሥራ በማሠራት ሕይወታቸው መራራ እንዲሆን አደረጉ።

ዘፀአት 1:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም ሁሉ፥ ያም ትውልድ ሁሉ። ነገር ግን የእስራኤል ትውልዶች ፍሬያማ ነበሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ እጅግም በረቱ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ እንዳይበዙ፥ ጦርነትም በተነሣብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ ኑ በጥበብ እንምከር።” በብርቱ ሥራ እንዲያስጨንቁአቸው ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራዓምሴስን የማከማቻ ከተሞች አድርገው ሠሩ። ነገር ግን በጨቆኑአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ሰፉ፤ ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። ግብፃውያንም እስራኤላውያንን በጭካኔ እንዲሠሩ አስገደዱአቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን አስመረሩት።