የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አስቴር 4:9-17

አስቴር 4:9-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሀታክም ተመልሶ መርዶክዮስ የነገረውን ሁሉ ለአስቴር አስታወቃት። እርሷም ለመርዶክዮስ እንዲህ እንዲለው ነገረችው፤ “የንጉሡ ባሮችና በንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገባ፣ ንጉሡ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለው ያውቃል፤ ይኸውም እንዲህ ያደረገው ሰው ይገደላል፤ አንድ ሰው ከእንዲህ ዐይነቱ ሞት የሚተርፈው፣ ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ሲዘረጋለት ብቻ ነው። እኔ ግን ወደ ንጉሡ ዘንድ እንድገባ ከተጠራሁ ከሠላሳ ቀን በላይ ሆነ።” የአስቴር ቃል ለመርዶክዮስ በተነገረው ጊዜ፣ ይህን መልስ ላከባት፤ “አንቺ በንጉሥ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ሕዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይመስልሽ፤ በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ፣ ለአይሁድ ርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” ከዚያም አስቴር ለመርዶክዮስ ይህን መልስ ላከችበት፤ “ሂድና በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ ስለ እኔም ጹሙልኝ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ለሦስት ቀን አትብሉ፤ አትጠጡም። እኔና ደንገጡሮቼም እናንተ እንደምታደርጉት ሁሉ እንጾማለን፤ ይህ ከተፈጸመ በኋላ ግን ነገሩ ምንም እንኳ ከሕግ ውጭ ቢሆንም፣ ወደ ንጉሡ ዘንድ እሄዳለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።” ስለዚህ መርዶክዮስ ሄደ፤ የአስቴርንም ትእዛዝ ሁሉ ፈጸመ።

አስቴር 4:9-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አክራትዮስም መጥቶ የመርዶክዮስን ቃል ለአስቴር ነገራት። አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፥ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው፦ የንጉሡ ባሪያዎችና በአገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር፥ እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፥ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም። አክራትዮስም የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ ነገረው። መርዶክዮስም አክራትዮስን፦ ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው፦ አንቺ፦ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፥ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመልስ አዘዘችው፦ ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፥ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን አትብሉም፥ አትጠጡም፥ እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፥ ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፥ ብጠፋም እጠፋለሁ። መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደረገ።

አስቴር 4:9-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሀታክም ይህን ሁሉ ፈጸመ፤ አስቴርም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለመርዶክዮስ እንዲነግር ሀታክን መልሳ ላከችው፤ “እንደሚታወቀው ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፥ ማንም ሰው ሳይጠራ ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ለመግባትና ንጉሡን ለማየት ቢሞክር በሞት ይቀጣል፤ እንግዲህ ሕጉ ይህ ሲሆን፥ ከንጉሡ አማካሪዎች እስከ ሕዝቡ ድረስ ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፤ በሕጉ መሠረት ከሞት ለመዳን የሚችለው ማንም ሰው ወደዚያ በሚገባበት ጊዜ ንጉሡ ፈቅዶ የወርቅ በትሩን ሲዘረጋለት ብቻ ነው፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ከተጠራሁ እነሆ ሠላሳ ቀኖች አልፈውኛል።” መርዶክዮስም የአስቴርን መልእክት ከተቀበለ በኋላ፥ ከዚህ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ላከባት፤ “አንቺ በቤተ መንግሥት ለመኖር በመቻልሽ ከሌሎች አይሁድ የተሻለ ዋስትና ያለሽ አይምሰልሽ፤ እንደዚህ ባለ ጊዜ ችላ ብለሽ ዝም ብትዪ፥ ለአይሁድ ከሌላ ቦታ ርዳታ መምጣቱ አይቀርም፤ እነርሱም በእርግጥ ይድናሉ፤ አንቺ ግን ትሞቻለሽ፤ የአባትሽም የቤተሰብ ሐረግ ተቋርጦ ይቀራል፤ ነገር ግን አንቺ ንግሥት የሆንሽው በዚህ መከራ ጊዜ እኛን ለመታደግ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” አስቴርም ለመርዶክዮስ እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “ሄደህ በሱሳ የሚገኙትን አይሁድ በአንድነት ሰብስብ፤ ጾም ዐውጃችሁም ለእኔ ጸልዩ፤ እስከ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም ዐይነት ምግብ አትብሉ፤ ምንም ዐይነት መጠጥ አትጠጡ፤ እኔና ደንገጡሮቼም በዚሁ ዐይነት እንቈያለን፤ ከዚህም በኋላ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ደፍሬ ወደ ንጉሡ ዘንድ እገባለሁ፤ ይህን በማድረጌ ብሞትም ልሙት።” መርዶክዮስም ተነሥቶ ሄደ፤ አስቴር በነገረችውም መሠረት ሁሉን ነገር አደረገ።