አስቴር 4:5-8
አስቴር 4:5-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች መካከል እርሷን እንዲያገለግል የተመደበውን ሀታክን ጠርታ፣ መርዶክዮስ ምን ችግር እንደ ገጠመውና ስለ ምንስ እንደዚህ እንደ ሆነ እንዲያጣራ ላከችው። ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው። አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው።
አስቴር 4:5-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አስቴርም ያገለግላት ዘንድ ንጉሡ ያቆመውን አክራትዮስን ጠራች እርሱም ከጃንደረቦች አንዱ ነበረ፥ እርስዋም ይህ ነገር ምንና ምን እንደ ሆነ ያስታውቃት ዘንድ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ አዘዘችው። አክራትዮስም በንጉሥ በር ፊት ወደ ነበረችው ወደ ከተማይቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ፥ አይሁድንም ለማጥፋት ሐማ በንጉሡ ግምጃ ቤት ይመዝን ዘንድ የተናገረውን የብሩን ቍጥር ነገረው። ለአስቴርም እንዲያሳያት ለመጥፋታቸው በሱሳ የተነገረውን የአዋጁን ጽሕፈት ቅጅ ሰጠው፥ ወደ ንጉሡም ገብታ ስለ ሕዝብዋ ትለምነውና ትማልደው ዘንድ እንዲነግራትና እንዲያዝዛት ነገረው።
አስቴር 4:5-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ አስቴር ከቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች መካከል በተለይ እርስዋን እንዲያገለግል ንጉሡ የመደበላትን ሀታክ የተባለውን ጠርታ ወደ መርዶክዮስ ዘንድ ሄዶ ምን እንደ ደረሰበት እንዲጠይቀው ላከችው። ሀታክም ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚያስገባው በር አጠገብ በሚገኘው የከተማይቱ አደባባይ ወደሚገኘው ወደ መርዶክዮስ ሄደ። መርዶክዮስም የደረሰበትን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገረው፤ ሃማን አይሁድ ሁሉ የሚገደሉለት ከሆነ ወደ ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት ምን ያኽል ገንዘብ ለማስገባት ቃል የገባለት መሆኑን ጭምር ገለጠለት። የአይሁድን ሕዝብ ለማስፈጀት በሱሳ ከተማ የተላለፈውን የዐዋጅ ቅጂም ለሀታክ ሰጠው፤ ይህንኑ የዐዋጅ ቅጂ ወስዶ ለአስቴር እንዲሰጣትና የሆነውንም ነገር ሁሉ እንዲገልጥላት፥ እንዲሁም ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝብዋ ምሕረትን እንድትለምን ይነግራት ዘንድ ሀታክን ለመነው።