የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አስቴር 4:1-11

አስቴር 4:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መርዶክዮስ የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም ማቅ ለብሶ፣ በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ አምርሮ እየጮኸ ወደ ከተማዪቱ መካከል ወጣ። ማቅ የለበሰ እንዲገባ ስለማይፈቀድለት፣ የሄደው እስከ ንጉሡ በር ድረስ ብቻ ነበር። የንጉሡ ዐዋጅና ትእዛዝ በደረሰበት አውራጃ ሁሉ፣ በአይሁድ መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ ጾሙ፤ አለቀሱ፤ ጮኹም። ብዙዎቹም ማቅና ዐመድ ላይ ተኙ። የአስቴር ደንገጡሮችና ጃንደረቦች መጥተው ስለ መርዶክዮስ በነገሯት ጊዜ፣ እጅግ ዐዘነች፤ እርሷም በማቁ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። ከዚያም አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች መካከል እርሷን እንዲያገለግል የተመደበውን ሀታክን ጠርታ፣ መርዶክዮስ ምን ችግር እንደ ገጠመውና ስለ ምንስ እንደዚህ እንደ ሆነ እንዲያጣራ ላከችው። ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው። አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው። ሀታክም ተመልሶ መርዶክዮስ የነገረውን ሁሉ ለአስቴር አስታወቃት። እርሷም ለመርዶክዮስ እንዲህ እንዲለው ነገረችው፤ “የንጉሡ ባሮችና በንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገባ፣ ንጉሡ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለው ያውቃል፤ ይኸውም እንዲህ ያደረገው ሰው ይገደላል፤ አንድ ሰው ከእንዲህ ዐይነቱ ሞት የሚተርፈው፣ ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ሲዘረጋለት ብቻ ነው። እኔ ግን ወደ ንጉሡ ዘንድ እንድገባ ከተጠራሁ ከሠላሳ ቀን በላይ ሆነ።”

አስቴር 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ አመድም ነሰነሰ፥ ወደ ከተማይቱም መካከል ወጣ፥ ታላቅም የመረረ ጩኸት ጮኸ። ማቅም ለብሶ በንጉሥ በር መግባት አይገባም ነበርና እስከ ንጉሡ በር አቅራቢያ መጣ። የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገር ሁሉ በአይሁድ ላይ ታላቅ ኀዘንና ጾም ልቅሶና ዋይታም ሆነ ብዙዎችም ማቅና አመድ አነጠፉ። የአስቴርም ደንገጥሮችዋና ጃንደረቦችዋ መጥተው ነገሩአት፥ ንግሥቲቱም እጅግ አዘነች፥ ማቁንም ለውጦ ልብስ ይለብስ ዘንድ ለመርዶክዮስ ሰደደችለት፥ እርሱ ግን አልተቀበለም። አስቴርም ያገለግላት ዘንድ ንጉሡ ያቆመውን አክራትዮስን ጠራች እርሱም ከጃንደረቦች አንዱ ነበረ፥ እርስዋም ይህ ነገር ምንና ምን እንደ ሆነ ያስታውቃት ዘንድ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ አዘዘችው። አክራትዮስም በንጉሥ በር ፊት ወደ ነበረችው ወደ ከተማይቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ፥ አይሁድንም ለማጥፋት ሐማ በንጉሡ ግምጃ ቤት ይመዝን ዘንድ የተናገረውን የብሩን ቍጥር ነገረው። ለአስቴርም እንዲያሳያት ለመጥፋታቸው በሱሳ የተነገረውን የአዋጁን ጽሕፈት ቅጅ ሰጠው፥ ወደ ንጉሡም ገብታ ስለ ሕዝብዋ ትለምነውና ትማልደው ዘንድ እንዲነግራትና እንዲያዝዛት ነገረው። አክራትዮስም መጥቶ የመርዶክዮስን ቃል ለአስቴር ነገራት። አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፥ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው፦ የንጉሡ ባሪያዎችና በአገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር፥ እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፥ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም።

አስቴር 4:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

መርዶክዮስም ስለ ተደረገው ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ከዚህም በኋላ ማቅ ለብሶና በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ አድርጎ እየጮኸ በመረረ ሁኔታ በማልቀስ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገባ። ማንም ሰው ማቅ ለብሶ ወደ ቤተ መንግሥት መግባት ስለማይፈቀድለት ወደ ቤተ መንግሥት መግቢያ በር ሲደርስ ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት አልቻለም። የንጉሡ ዐዋጅ በተላለፈባቸው አገሮች ሁሉ በአይሁድ መካከል ከፍተኛ የለቅሶ ጩኸት ተሰማ፤ እነርሱም መጾምና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ፤ አብዛኞቹም ማቅ ለብሰውና በራሳቸው ላይ ዐመድ ነስንሰው ተቀመጡ። የአስቴር ደንገጡሮችና እርስዋን የሚጠብቁ ጃንደረቦች መርዶክዮስ የሚያደርገውን ሁሉ በነገሩአት ጊዜ ጥልቅ ሐዘን ተሰማት፤ ለመርዶክዮስም በማቅ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልቀበልም አለ። ከዚህም በኋላ አስቴር ከቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች መካከል በተለይ እርስዋን እንዲያገለግል ንጉሡ የመደበላትን ሀታክ የተባለውን ጠርታ ወደ መርዶክዮስ ዘንድ ሄዶ ምን እንደ ደረሰበት እንዲጠይቀው ላከችው። ሀታክም ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚያስገባው በር አጠገብ በሚገኘው የከተማይቱ አደባባይ ወደሚገኘው ወደ መርዶክዮስ ሄደ። መርዶክዮስም የደረሰበትን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገረው፤ ሃማን አይሁድ ሁሉ የሚገደሉለት ከሆነ ወደ ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት ምን ያኽል ገንዘብ ለማስገባት ቃል የገባለት መሆኑን ጭምር ገለጠለት። የአይሁድን ሕዝብ ለማስፈጀት በሱሳ ከተማ የተላለፈውን የዐዋጅ ቅጂም ለሀታክ ሰጠው፤ ይህንኑ የዐዋጅ ቅጂ ወስዶ ለአስቴር እንዲሰጣትና የሆነውንም ነገር ሁሉ እንዲገልጥላት፥ እንዲሁም ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝብዋ ምሕረትን እንድትለምን ይነግራት ዘንድ ሀታክን ለመነው። ሀታክም ይህን ሁሉ ፈጸመ፤ አስቴርም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለመርዶክዮስ እንዲነግር ሀታክን መልሳ ላከችው፤ “እንደሚታወቀው ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፥ ማንም ሰው ሳይጠራ ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ለመግባትና ንጉሡን ለማየት ቢሞክር በሞት ይቀጣል፤ እንግዲህ ሕጉ ይህ ሲሆን፥ ከንጉሡ አማካሪዎች እስከ ሕዝቡ ድረስ ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፤ በሕጉ መሠረት ከሞት ለመዳን የሚችለው ማንም ሰው ወደዚያ በሚገባበት ጊዜ ንጉሡ ፈቅዶ የወርቅ በትሩን ሲዘረጋለት ብቻ ነው፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ከተጠራሁ እነሆ ሠላሳ ቀኖች አልፈውኛል።”