አስቴር 1:13-22
አስቴር 1:13-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕግንና ፍትሕን በተመለከተ የሊቃውንቱን ምክር መጠየቅ በንጉሥ ዘንድ የተለመደ ነበርና፣ ስለ ዘመናት ሁኔታ ዕውቀት ካላቸው ጠቢባን ጋራ ተነጋገረበት፤ እነዚህ አርቄስዮስ፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሺሽ፣ ሜሬስ፣ ማሌሴዓር፣ ምሙካ የተባሉ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት በንጉሡ ዘንድ የተለየ ስፍራና በመንግሥቱም አመራር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ነበሩ። ንጉሡም፣ “በጃንደረቦቹ በኩል የተላከባትን የንጉሥ ጠረክሲስን ትእዛዝ ስላልፈጸመች፣ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም ምሙካ በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን፣ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ጭምር ነው። ይህ የንግሥቲቱ አድራጎት በሌሎቹ ሁሉ ዘንድ ስለሚሰማ፣ ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ‘ንጉሥ ጠረክሲስ ንግሥት አስጢን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያዛትም፣ እርሷ ግን መሄድ አልፈለገችም’ ይላሉ። በዚህች በዛሬዪቱም ዕለት የንግሥቲቱን አድራጎት የሰሙ የፋርስና የሜዶን መኳንንት ሚስቶች፣ ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሊመልሱ ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ማብቂያ የሌለው ንቀትና ጠብ ይፈጠራል። “ስለዚህ ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘው ከሆነ፣ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ ጠረክሲስ ዘንድ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ እንዳትገባ ንጉሣዊ ዐዋጅ ይውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ይጻፍ፤ እንዲሁም ንጉሡ የእቴጌነቷን ክብር ከርሷ ለምትሻል ለሌላዪቱ ይስጥ። ከዚያም የንጉሡ ዐዋጅ በሰፊው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉት ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።” ንጉሡና መኳንንቱ ሁሉ በዚህ ምክር ተደሰቱ፤ ንጉሡም ምሙካ ያቀረበውን ሐሳብ በሥራ ላይ አዋለው። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ቤተ ሰብ ላይ ገዥ እንዲሆን መልእክት አስተላለፈ፤ መልእክቱም ለየአውራጃዎቹ በየራሳቸው ጽሑፍና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ ተጽፎ በግዛቱ ሁሉ ተበተነ።
አስቴር 1:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕግንና ፍርድን በሚያውቁ ሁሉ ፊት የንጉሡ ወግ እንዲህ ነበረና ንጉሡ የዘመኑን ነገር የሚያውቁትን ጥበበኞችን፥ በመንግሥቱም ቀዳሚዎች ሆነው የሚቀመጡ የንጉሡ ባለምዋሎች ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓር፥ ምሙካን በአጠገቡ ሳሉ፦ በጃንደረቦች እጅ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትእዛዝ ስላላደረገች በንግሥቲቱ በአስጢን ላይ እንደ ሕጉ የምናደርገው ምንድር ነው? አላቸው። ምሙካንም በንጉሡና በአዛውንቱ ፊት እንዲህ አለ፦ ንግሥቲቱ አስጢን አዛውንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ አገር ያሉትን አሕዛብ ሁሉ በድላለች እንጂ ንጉሡን ብቻ የበደለች አይደለችም። ይህ የንግሥቲቱ ነገር ወደ ሴቶች ሁሉ ይደርሳልና፦ ንጉሡ አርጤክስስ ንግሥቲቱ አስጢን ወደ እርሱ ትገባ ዘንድ አዘዘ፥ እርስዋ ግን አልገባችም ተብሎ በተነገረ ጊዜ ባሎቻቸው በዓይናቸው ዘንድ የተናቁ ይሆናሉ። ዛሬም የንግሥቲቱን ነገር የሰሙት የፋርስና የሜዶን ወይዛዝር እንዲህና እንዲህ ብለው ለንጉሡ አዛውንት ሁሉ ይናገራሉ፥ ንቀትና ቍጣም ይበዛል። ንጉሡም ቢፈቅድ፥ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ፊት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትገባ የንጉሡ ትእዛዝ ከእርሱ ይውጣ፥ እንዳይፈርስም በፋርስና በሜዶን ሕግ ይጻፍ፥ ንጉሡም ንግሥትነትዋን ከእርስዋ ለተሻለችው ለሌላይቱ ይስጥ። የንጉሡም ትእዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ታላቁንም ታናሹንም ያከብራሉ። ይህም ምክር ንጉሡንና አዛውንቱን ደስ አሰኛቸው፥ ንጉሡም እንደ ምሙካን ቃል አደረገ። ሰው ሁሉ በቤቱ አለቃ ይሁን፥ በሕዝቡም ቋንቋ ይናገር ብሎ ለአገሩ ሁሉ እንደ ጽሕፈቱ ለሕዝቡም ሁሉ እንደ ቋንቋው ደብዳቤዎችን ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ሰደደ።
አስቴር 1:13-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕግና ባህልን በሚመለከት ጉዳይ፥ ብልኅ አማካሪዎችን መጠየቅ በንጉሡ ዘንድ የተለመደ ነገር ስለ ነበር፥ በዚህም ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባው ይመክሩት ዘንድ አማካሪዎቹን አስጠራ። ዘወትር የሚያማክሩትም ካርሸና፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ታርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማርሰናና መሙካን ተብለው የሚጠሩ በመንግሥቱ አመራር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰባቱ የፋርስና የሜዶን ሹማምንት ነበሩ። ንጉሡም እነዚህን አማካሪዎች “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ያመጡ ዘንድ በማዘዝ አገልጋዮቼን ብልክባት እርስዋ እምቢ ብላ ቀርታለች! ታዲያ፥ በእርስዋ ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ሕጉ ምን ይላል?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚህ በኋላ ከአማካሪዎቹ አንዱ የሆነው መሙካን እንዲህ ሲል የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፤ “በመሠረቱ ንግሥት አስጢን ያዋረደችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና እንዲያውም በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ጭምር ነው። ከእንግዲህ ወዲህ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ የምትኖር ማንኛዋም ሴት፥ ንግሥት አስጢን ያደረገችውን ሁሉ ስትሰማ ባልዋን በንቀት ዐይን መመልከት ትጀምራለች፤ እነርሱም በበኩላቸው ‘ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያስጠራት እምቢ ብላው ቀርታ የለምን?’ ይላሉ። የፋርስና የሜዶን መንግሥት ባለሥልጣኖች ሚስቶች ይህን ንግሥቲቱ የፈጸመችውን አሳፋሪ ድርጊት በሚሰሙበት ጊዜ ዛሬውኑ ፀሐይ ሳትጠልቅ በባሎቻቸው ላይ መዘባነን ይጀምራሉ፤ በየሀገሩ የሚገኙ ሚስቶችም ባሎቻቸውን ማክበርን ይተዋሉ፤ ባሎችም ከሚስቶቻቸው ጋር መጣላት ሊኖርባቸው ነው። ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ መልካም ፈቃድህ ቢሆን፥ ንግሥት አስጢን ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ ፊት መቅረብ ከቶ እንዳይፈቀድላት የሚገልጥ ውሳኔህን በዐዋጅ አስተላልፍ፤ ይህም ውሳኔ ከቶ የማይለወጥ ሆኖ ለዘለዓለም ይጸና ዘንድ በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ እንዲመዘገብ ትእዛዝ አስተላልፍ፤ የአስጢንንም የንግሥትነት ማዕርግ ከእርስዋ ለተሻለች ለሌላ ሴት ስጥ። አንተ የምታስተላልፈውም ዐዋጅ እጅግ ታላቅ በሆነው በዚህ በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ሁሉ በይፋ በሚነገርበት ጊዜ እያንዳንድዋ ሴት ባለጸጋም ይሁን ወይም ድኻ ባልዋን በአክብሮት ትመለከታለች።” ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ይህን ሐሳብ በደስታ ተቀበሉት፤ ንጉሡም መሙካን ያቀረበውን ምክር በሥራ ላይ አዋለ። ስለዚህም ንጉሡ “እያንዳንዱ ባል የቤቱ አባወራ ሆኖ በአዛዥነት የመናገር መብቱ የተጠበቀ ይሁን!” የሚል ትእዛዝ በየቋንቋውና በየአጻጻፍ ሥርዓቱ ተዘጋጅቶ ወደያንዳንዱ አገር እንዲተላለፍ አደረገ።