ኤፌሶን 4:3-32

ኤፌሶን 4:3-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በአ​ንድ መን​ፈ​ስና በሰ​ላም ማሰ​ሪ​ያ​ነት እየ​ተ​ጠ​በ​ቃ​ችሁ፥ ለአ​ንዱ ተስ​ፋ​ችሁ እንደ መጠ​ራ​ታ​ችሁ መጠን፥ አንድ አካ​ልና አንድ መን​ፈስ ትሆኑ ዘንድ እማ​ል​ዳ​ች​ኋ​ለሁ። ጌታ አንድ ነው፤ ሃይ​ማ​ኖ​ትም አን​ዲት ናት፤ ጥም​ቀ​ትም አን​ዲት ናት። በሁሉ ሙሉ የሚ​ሆን ሁሉም ከእ​ርሱ የተ​ገኘ ከሁ​ሉም በላይ ያለ የሁሉ አባት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አንድ ነው። ከእኛ ለእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ በክ​ር​ስ​ቶስ ስጦታ መጠን ጸጋው ተሰ​ጥ​ቶ​ናል። “ምር​ኮን ማር​ከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋ​ህ​ንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላ​ልና። ከም​ድር በታች ካል​ወ​ረደ መው​ጣቱ ምን​ድን ነው? የወ​ረ​ደው እርሱ ነው፤ ሁሉ​ንም ይመላ ዘንድ ከሰ​ማ​ያት ሁሉ በላይ የወ​ጣው ደግሞ እርሱ ነው። እር​ሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተ ሰቦ​ቹም ሐዋ​ር​ያ​ትን፥ ከእ​ነ​ር​ሱም ነቢ​ያ​ት​ንና የወ​ን​ጌል ሰባ​ኪ​ዎ​ችን፥ ጠባ​ቂ​ዎ​ች​ንና መም​ህ​ራ​ንን ሾመ። ቅዱ​ሳን ለአ​ገ​ል​ግ​ሎቱ ሥራና ለክ​ር​ስ​ቶስ አካል ሕንጻ እን​ዲ​ጸኑ፤ ሁላ​ችን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ልጅ በማ​መ​ንና በማ​ወቅ አንድ እስ​ክ​ን​ሆን ድረስ በክ​ር​ስ​ቶስ ምል​ዐት መጠን፥ አካለ መጠን እንደ አደ​ረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስ​ክ​ን​ሆን ድረስ፥ እን​ግ​ዲህ በሽ​ን​ገ​ላ​ቸው ያስቱ ዘንድ በሚ​ተ​ና​ኰሉ ሰዎች ተን​ኰል ምክ​ን​ያት በት​ም​ህ​ርት ነፋስ ሁሉ ወዲ​ያና ወዲህ እየ​ተ​ፍ​ገ​መ​ገ​ም​ንና እየ​ተ​ን​ሳ​ፈ​ፍን ሕፃ​ናት አን​ሁን። ነገር ግን በፍ​ቅር እው​ነ​ተ​ኞች እን​ሆን ዘንድ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወደ ክር​ስ​ቶስ እን​ደግ። ከእ​ርሱ የተ​ነሣ አካል ሁሉ እያ​ን​ዳ​ንዱ ክፍል በልክ እን​ደ​ሚ​ሠራ፥ በተ​ሰ​ጠው በሥር ሁሉ እየ​ተ​ጋ​ጠ​መና እየ​ተ​ያ​ያዘ፥ ራሱን በፍ​ቅር ለማ​ነጽ አካ​ሉን ያሳ​ድ​ጋል። እን​ግ​ዲህ በል​ባ​ቸው ከንቱ አሳብ እን​ደ​ሚ​ኖሩ እንደ አሕ​ዛብ እን​ዳ​ት​ኖሩ ይህን እላ​ለሁ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እመ​ሰ​ክ​ራ​ለሁ። ልቡ​ና​ቸው የተ​ጨ​ፈነ ነው፤ በስ​ን​ፍ​ና​ቸ​ውና በድ​ን​ቍ​ር​ና​ቸው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከሚ​ሰ​ጣ​ቸው ሕይ​ወት የተ​ለዩ ናቸው። ተስፋ የቈ​ረጡ ናቸው፤ ራሳ​ቸ​ው​ንም ለጕ​ስ​ቍ​ልና፥ ለር​ኵ​ሰ​ትና ለመ​ዳ​ራት አሳ​ል​ፈው ሰጡ። እና​ንተ ግን ክር​ስ​ቶ​ስን የተ​ማ​ራ​ች​ሁት እን​ደ​ዚህ አይ​ደ​ለም። በር​ግጥ ከሰ​ማ​ች​ሁት፥ እው​ነት በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ነውና እው​ነ​ትን በእ​ርሱ ዘንድ ትማ​ራ​ላ​ችሁ፤ የቀ​ድሞ ጠባ​ያ​ች​ሁን ከእ​ና​ንተ አርቁ፤ ይህ​ንም ስሕ​ተት በሚ​ያ​መ​ጣው ምኞት ስለ​ሚ​ጠ​ፋው ስለ አሮ​ጌው ሰው​ነት እላ​ለሁ። የል​ቡ​ና​ች​ሁን ዕው​ቀት አድሱ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ው​ነት፥ በቅ​ን​ነ​ትና በን​ጽ​ሕና ያደ​ሰ​ውን አዲ​ሱን ሰው​ነት ልበ​ሱት። ስለ​ዚ​ህም ሐሰ​ትን ተዉ​አት፤ ሁላ​ች​ሁም ከወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ችሁ ጋር እው​ነ​ትን ተነ​ጋ​ገሩ፤ እኛ አንድ አካል ነንና። ተቈጡ፤ አት​በ​ድ​ሉም፤ ፀሐይ ሳይ​ጠ​ል​ቅም ቍጣ​ች​ሁን አብ​ርዱ። ለሰ​ይ​ጣ​ንም መን​ገ​ድን አት​ስ​ጡት። የሚ​ሰ​ር​ቅም እን​ግ​ዲህ አይ​ስ​ረቅ፤ ነገር ግን ድሃ​ውን ይረዳ ዘንድ በእ​ጆቹ መል​ካም እየ​ሠራ ይድ​ከም። የሚ​ሰ​ሙ​አ​ችሁ ሞገ​ስን ያገኙ ዘንድ፥ ግዳ​ጃ​ችሁ እን​ዲ​ፈ​ጸም መል​ካም ነገር እንጂ ክፉ ነገር ሁሉ ከአ​ፋ​ችሁ አይ​ውጣ። በዳ​ና​ችሁ ጊዜ የታ​ተ​ማ​ች​ሁ​በ​ትን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቅዱስ መን​ፈስ አታ​ሳ​ዝ​ኑት። መራ​ራ​ነ​ት​ንና ቍጣን፥ ብስ​ጭ​ት​ንና ርግ​ማ​ንን፥ ጥፋ​ት​ንና ስድ​ብን ሁሉ ከክፉ ነገር ሁሉ ጋር ከእ​ና​ንተ አርቁ። እርስ በር​ሳ​ች​ሁም ቸሮ​ችና ርኅ​ሩ​ኆች ሁኑ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በክ​ር​ስ​ቶስ ይቅር እን​ዳ​ላ​ችሁ ይቅር ተባ​ባሉ።

ኤፌሶን 4:3-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።” ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ከርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል። ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም። እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቡናቸው ጨልሟል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል። ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኩሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤ በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በርሱ ተምራችኋል። ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ ደግሞም በአእምሯችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና። “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤” በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም። እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ። ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋራ ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።

ኤፌሶን 4:3-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።

ኤፌሶን 4:3-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሰላም ተሳስራችሁ ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚገኘውን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ። እንዲሁም አንድ ጌታ፥ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። ነገር ግን ክርስቶስ ለመስጠት በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን የጸጋው ስጦታ ተሰጥቶናል። ይህም፦ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ብዙ ምርኮኞችን ይዞ ሄደ፤ ለሰዎችም ስጦታዎችን ሰጠ” እንደ ተባለው ነው። ታዲያ፥ ይህ “ወደ ላይ ወጣ” የሚለው ቃል አስቀድሞ ወደዚህች ምድር፥ ከምድሪቱም ወደ ዝቅተኛው ቦታ መውረዱ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንን ያመለክታል? ይህ ወደ ታች የወረደው ደግሞ ያ ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ነው። እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ አንዳንዶቹ ነቢያት፥ አንዳንዶቹ የወንጌል ሰባኪዎች፥ አንዳንዶቹ የምእመናን እረኞች፥ አንዳንዶቹ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ስጦታዎችን ሰጣቸው። ይህንንም ያደረገው የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ፥ ምእመናንን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ለማዘጋጀት ነው። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ በእምነት ወደሚገኘው አንድነት ደርሰን፥ ክርስቶስ ፍጹምና ሙሉ እንደሆነው ዐይነት እኛም ሙሉ ሰው እንድንሆን ነው። ከእንግዲህ ወዲህ በሰዎች የተንኰል ሽንገላና አታላይነት በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስና ሞገድ ወዲያና ወዲህ ተገፍትረው እንደሚወሰዱ ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን በሁሉም ነገር ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እናድጋለን። የተለያዩት የሰውነት ክፍሎች የሚገጣጠሙት በክርስቶስ ነው፤ አካልም በሙሉ የተያያዘው በመገጣጠሚያዎቹ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተመደበለትን ተግባር በሚገባ ሲያከናውን አካል በሙሉ ያድጋል፤ በፍቅርም ይታነጻል። ከእንግዲህ ወዲህ ሐሳባቸው ከንቱ እንደሆነው እንደ አሕዛብ አትኑሩ ብዬ በጌታ ስም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ የእነርሱ አእምሮ ጨልሞአል፤ ባለማወቃቸውና በእልኸኛነታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ከሚሰጠው ሕይወት ተለይተዋል። የዕፍረት ስሜታቸው ስለ ጠፋ ርኲሰቶችን ሁሉ ለመፈጸም ራሳቸውን ለሥጋዊ ምኞታቸው አሳልፈው ሰጥተዋል። እናንተ ግን ስለ ክርስቶስ የተማራችሁት እንዲህ አይደለም። በእርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስ ባለው እውነት መሠረትም ከእርሱ ተምራችኋል። ስለዚህ አታሎ ወደ ኃጢአት በሚመራ ምኞት የተበላሸውን አስቀድሞ ትኖሩበት የነበረውን፥ አሮጌውን የተፈጥሮ ባሕርይ አስወግዱ። አእምሮአችሁም በመንፈስ ይታደስ። በእውነተኛ ጽድቅና ቅድስና በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት ልበሱ። ስለዚህ ውሸት አትናገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ስለ ሆንን እርስ በርሳችን እውነት እንናገር። ተቈጡ! በቊጣችሁ ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ቊጣችሁም ሳይወገድ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ። ለዲያብሎስም መግቢያ ቀዳዳ አትስጡት። ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ ወዲያ አይስረቅ፤ ይልቅስ ለችግረኞች ይሰጥ ዘንድ ገንዘብ እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካም ነገርን ይሥራ። ከቶ ከአፋችሁ ክፉ ቃል አይውጣ፤ ነገር ግን ለሚሰሙት ደስ የሚያሰኝና ለማነጽ የሚጠቅም ለሰዎችም አስፈላጊ የሆነውን ቃል ተናገሩ። ለምትዋጁበት ቀን ማረጋገጫ እንዲሆናችሁ የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ። መራራነት፥ ንዴት፥ ቊጣ፥ ሁከት፥ ስድብና ማናቸውም ዐይነት ክፋት ሁሉ ከእናንተ ወዲያ ይራቅ። ይልቅስ እርስ በርሳችሁ ደጎችና አዛኞች ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ።

ኤፌሶን 4:3-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ፤” ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም የክርስቶስ አካል ለመገንባት፥ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ነው፤ ይህም ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ መላው አካል በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፥ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። እንግዲህ አሕዛብ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ፥ በጌታም እለምናችኋለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸውና በልባቸው ደንዳንነት ምክንያት፥ ልቡናቸው ጨለመ፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ፥ በማይረካ ምኞት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ለሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፤ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ስለ ቀድሞ አኗኗሯችሁም፥ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውንና የተበላሸውን፥ አሮጌ ሰው አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን የሰውነት አካሎች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ፥ ኃጢአትን ግን አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። እንደ አስፈላጊነቱ፥ ለሚሰሙት ጸጋን እንዲሰጥ፥ ለማነጽ የሚጠቅም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም፥ ጩኸትና ስድብን ሁሉ፥ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።