ኤፌሶን 4:11-16
ኤፌሶን 4:11-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተ ሰቦቹም ሐዋርያትን፥ ከእነርሱም ነቢያትንና የወንጌል ሰባኪዎችን፥ ጠባቂዎችንና መምህራንን ሾመ። ቅዱሳን ለአገልግሎቱ ሥራና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ እንዲጸኑ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ምልዐት መጠን፥ አካለ መጠን እንደ አደረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስክንሆን ድረስ፥ እንግዲህ በሽንገላቸው ያስቱ ዘንድ በሚተናኰሉ ሰዎች ተንኰል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ ወዲያና ወዲህ እየተፍገመገምንና እየተንሳፈፍን ሕፃናት አንሁን። ነገር ግን በፍቅር እውነተኞች እንሆን ዘንድ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ። ከእርሱ የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠው በሥር ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
ኤፌሶን 4:11-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ከርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።
ኤፌሶን 4:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
ኤፌሶን 4:11-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ አንዳንዶቹ ነቢያት፥ አንዳንዶቹ የወንጌል ሰባኪዎች፥ አንዳንዶቹ የምእመናን እረኞች፥ አንዳንዶቹ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ስጦታዎችን ሰጣቸው። ይህንንም ያደረገው የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ፥ ምእመናንን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ለማዘጋጀት ነው። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ በእምነት ወደሚገኘው አንድነት ደርሰን፥ ክርስቶስ ፍጹምና ሙሉ እንደሆነው ዐይነት እኛም ሙሉ ሰው እንድንሆን ነው። ከእንግዲህ ወዲህ በሰዎች የተንኰል ሽንገላና አታላይነት በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስና ሞገድ ወዲያና ወዲህ ተገፍትረው እንደሚወሰዱ ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን በሁሉም ነገር ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እናድጋለን። የተለያዩት የሰውነት ክፍሎች የሚገጣጠሙት በክርስቶስ ነው፤ አካልም በሙሉ የተያያዘው በመገጣጠሚያዎቹ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተመደበለትን ተግባር በሚገባ ሲያከናውን አካል በሙሉ ያድጋል፤ በፍቅርም ይታነጻል።
ኤፌሶን 4:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም የክርስቶስ አካል ለመገንባት፥ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ነው፤ ይህም ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ መላው አካል በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፥ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።