ኤፌሶን 4:1-8
ኤፌሶን 4:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለተጠራሁላት አጠራር በሚገባ ትኖሩ ዘንድ በክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ እማልዳችኋለሁ። በፍጹም የዋህነት ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ እየታገሣችሁ፥ ለወንድሞቻችሁም እሺ እያላችሁ፥ በፍቅር እየተጋችሁና እየተባበራችሁ፥ በአንድ መንፈስና በሰላም ማሰሪያነት እየተጠበቃችሁ፥ ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን፥ አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኋለሁ። ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖትም አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት። በሁሉ ሙሉ የሚሆን ሁሉም ከእርሱ የተገኘ ከሁሉም በላይ ያለ የሁሉ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው። ከእኛ ለእያንዳንዱ በክርስቶስ ስጦታ መጠን ጸጋው ተሰጥቶናል። “ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋህንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላልና።
ኤፌሶን 4:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮ ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።”
ኤፌሶን 4:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
ኤፌሶን 4:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ጌታን በማገልገሌ እስረኛ የሆንኩ እኔ፥ ለተጠራችሁበት ጥሪ ተገቢ የሆነ ሕይወት ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። በፍቅር እርስ በርሳችሁ እየታገሣችሁ ዘወትር በትሕትና በገርነትና በመቻቻል ኑሩ። በሰላም ተሳስራችሁ ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚገኘውን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ። እንዲሁም አንድ ጌታ፥ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። ነገር ግን ክርስቶስ ለመስጠት በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን የጸጋው ስጦታ ተሰጥቶናል። ይህም፦ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ብዙ ምርኮኞችን ይዞ ሄደ፤ ለሰዎችም ስጦታዎችን ሰጠ” እንደ ተባለው ነው።
ኤፌሶን 4:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ እንድትመላለሱ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትናና በየዋህነት ሁሉ፥ በትዕግሥትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ፤” ይላል።