ኤፌሶን 1:3-15
ኤፌሶን 1:3-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን። ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፥ ንጹሓንና ያለ ነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን። በኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ውድ ፈቃዱ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በሚወደው ልጁ የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ። በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኀጢአታችንም ተሰረየልን። ይኸውም በፍጹም ጥበብና ምክር ለእኛ አብዝቶ ያደረገው ነው። እንደ ወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን። የሚደርስበትንም ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን። ይኸውም አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ልትድኑበት የተማራችሁትን የእውነት ቃል ሰምታችሁና አምናችሁ፤ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ። ይኸውም ለጌትነቱ ክብር የርስታችን መያዣ፥ የሕይወታችንም ቤዛነት ነው። ስለዚህም እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁን፥ ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ሰምቼ፥
ኤፌሶን 1:3-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን፤ ይኸውም፣ በሚወድደው በእርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው። በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤ ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ፣ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው። ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ፣ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በእርሱ ተመርጠናል፤ ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል። አምናችሁም በእርሱ በመሆን፣ ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል። ለክብሩ ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ፣ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው። ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነት፣ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንሥቶ፣
ኤፌሶን 1:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥
ኤፌሶን 1:3-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰማይ ባለው መንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን። ቅዱሳንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን በፊቱ እንድንገኝ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ መረጠን። እግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ሆኖ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ በፍቅሩ መረጠን። ይህንንም ያደረገው በተወደደው ልጁ አማካይነት በነጻ የሰጠን ክቡር ጸጋ እንዲመሰገን ነው። ከእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት የተነሣ በልጁ ደም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን። ጸጋውንም በጥበብና በዕውቀት ሁሉ አብዝቶ አፈሰሰልን። እግዚአብሔር በቸርነቱ በክርስቶስ አማካይነት አስቀድሞ ባቀደው መሠረት የፈቃዱን ምሥጢር እንድናውቅ አደረገ። ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር በሥራ ላይ የሚያውለው ዕቅድ በሰማይና በምድር ያሉት ፍጥረቶች ሁሉ ተጠቃለው በአንዱ በክርስቶስ ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ነው። ሁሉን ነገር በራሱ ፈቃድ የሚሠራ እግዚአብሔር አስቀድሞ በዐቀደልን መሠረት በክርስቶስ አማካይነት የእርሱ ወገኖች እንድንሆን መረጠን። ይህም የሆነው ክርስቶስን ተስፋ በማድረግ መጀመሪያዎች የሆንነው የእግዚአብሔርን ክብር በምስጋና እንድንገልጥ ነው። እናንተም የመዳናችሁ መልካም ዜና የሆነውን የእውነት ቃል በሰማችሁ ጊዜ በክርስቶስ አምናችኋል፤ እንዲሁም እርሱ ሊሰጣችሁ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል። ይህ መንፈስ ለክብሩ ምስጋና እንዲሆን እግዚአብሔር የራሱ የሆኑትን በሙሉ እስኪዋጅ ድረስ ልናገኝ ላለው ርስታችን መያዣችን ነው። ስለዚህ በጌታ በኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምቼ
ኤፌሶን 1:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በሰማያዊ ስፍራ በክርስቶስ የባረከን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር፥ በፍቅር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እድንሆን በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም በነጻ የሰጠን የከበረ ጸጋው እንዲመሰገን ይህን አደረገ። በእርሱም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን፥ በደሙ ቤዛነታችንን አገኘን፤ የበደላችንም ይቅርታ ሆነ። ጸጋውንም አበዛልን። በጥበብና በአእምሮ ሁሉ፥ በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል፤ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው፥ እንደ ፈቃዱና እንደ ምክሩ ሁሉን የሚያከናውን እንደ እርሱ ዓላማ የተወሰንን በክርስቶስ በርስትነት ተቀበልን። ይኸውም በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ደግሞ ለክብሩ ምስጋና እንድንሆን ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፥ በክርስቶስም አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም ለክብሩ ምስጋና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ የርስታችን መያዣ ነው። እኔ ደግሞ፥ በጌታ ኢየሱስ ለቅዱሳኖች ሁሉ ያላችሁን እምነትና ፍቅር ሰምቻለሁ፤ በዚህም ምክንያት፥