ዘዳግም 9:22-29
ዘዳግም 9:22-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሐታአዋ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አስቈጣችሁት። እግዚአብሔር (ያህዌ) ከቃዴስ በርኔ ባስወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም። እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ። እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤ እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ (አዶናይ ያህዌ) በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ። ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን ዐስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት። አለዚያ እኛን ካመጣህበት ምድር ያሉ ሰዎች ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያገባቸው ስላልቻለና ስለ ጠላቸው፣ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ ይላሉ። ነገር ግን እነርሱ በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።”
ዘዳግም 9:22-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“በውዕየት፥ በፈተናም በምኞት መቃብርም እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። እግዚአብሔርም፦ ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፤ በእርሱም አላመናችሁም፤ ቃሉንም አልሰማችሁም። ለእናንተ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዐመፀኞች ነበራችሁ። “እግዚአብሔርም፦ ያጠፋችሁ ዘንድ ስለ ተናገረ ቀድሞ እንደ ለመንሁ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ለመንሁ። በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ የአማልክት ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህ የተቤዠሃቸውን፥ በጠነከረችውም እጅህና በተዘረጋች ክንድህ ከግብፅ ያወጣሃቸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። በራስህ የማልህላቸውን አገልጋዮችህን አብርሃምንና ይስሐቅን፥ ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፥ ክፋቱንም፥ ኀጢአቱንም አትመልከት፤ ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች፦ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። እነርሱም በታላቅ ኀይልህ፥ በጸናውና በተዘረጋውም ክንድህ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።
ዘዳግም 9:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በተቤራም በማሳህም በምኞት መቃብርም እግዚአብሔርን አስቆጣችሁት። እግዚአብሔርም፦ ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ድምፁንም አልሰማችሁም። እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዓመፀኞች ነበራችሁ። እግዚአብሔርም፦ አጠፋችኋለሁ ብሎ ስለ ተናገረ በወደቅሁበት ዘመን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ወደቅሁ። በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅነትህ የተቤዠኸውን፥ በጠነከረችውም እጅ ከግብፅ ያወጣኸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ደንዳንነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት፤ ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች፦ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። እነርሱም በታላቅ ኃይልህ በተዘረጋውም ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።
ዘዳግም 9:22-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እንደገናም በታብዔራ፥ በማሳህና በቂብሮት ሐታዋ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። እግዚአብሔር፥ ‘ሂዱ፤ የሰጠኋችሁንም የተስፋ ምድር ውረሱ’ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁም ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፃችሁ እንጂ አልተማመናችሁበትም፤ ለቃሉም አልታዘዛችሁም። እኔ ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ። “ከዚያም ሁሉ የተነሣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ ይህንንም ያደረግኹት እርሱ ‘እደመስሳችኋለሁ’ ብሎ ስለ ነበር ነው፤ እንዲህም ብዬ ጸለይኩ፥ ‘ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህና ብርታትህ ዋጅተህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን የራስህን ሕዝብ አታጥፋ፤ አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ የዚህን ሕዝብ እልኸኛነት፥ ክፋትና ኃጢአት ሁሉ አትቊጠርበት፤’ ይህ ባይሆን ግን፦ ‘እግዚአብሔር በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡን ወደዚያች ምድር ሊያስገባቸው አልቻለም’ ብለው ግብጻውያን መዘባበት ይጀምራሉ፤ እንዲያውም፦ ‘ሕዝቡን ስለ ጠላቸው ሊገድላቸው ፈልጎ ወደ በረሓ አወጣቸው’ ይሉሃል። ከዚህም ሁሉ በላይ ይህ ሕዝብ ለራስህ ወገን እንዲሆን የመረጥከውና በታላቁ ኀይልህና ብርታትህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ነው።”
ዘዳግም 9:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እንደገና በታቤራ፥ በማሳህም፥ በቂብሮት ሐታዋም ጌታን አስቆጣችሁት። ጌታም፥ ‘ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ’ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በጌታ በአምላካችሁ ቃል ላይ ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ለቃሉም አልታዛችሁም። እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በጌታ ላይ ዓመፀኞች ነበራችሁ። “አጠፋችኋለሁ፥ ብሎ ጌታም ስለ ተናገረ፥ በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በጌታ ፊት ወደቅሁ። በጌታም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ ‘ጌታ አምላኬ ሆይ፥ በታላቅነትህ የተቤዠኸውን፥ በጠነከረችውም እጅ ከግብጽ ያወጣኸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። ባርያዎችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብንም አስብ፥ የዚህን ሕዝብ ደንዳንነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት፥ እኛን ከእርሷ ያወጣህባት ምድር ሰዎች፥ ጌታ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያስገባቸው ስላልቻለ፥ ስለ ጠላቸውም፥ ወደ ምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ እንዳይሉ። እነርሱም በታላቅ ኃይልህ በተዘረጋውም ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና።”