ዘዳግም 8:2-6
ዘዳግም 8:2-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ። ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፤ አንተም ያላወቅኸውን፥ አባቶችህም ያላወቁትን መና መገበህ። የለበስኸው ልብስ አላረጀም፤ እግርህም አልነቃም፤ እነሆ፥ አርባ ዓመት ሆነ። ሰውም ልጁን እንደሚገሥጽ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ ዕወቅ። በመንገዱም እንድትሄድ፥ እርሱንም እንድትፈራ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።
ዘዳግም 8:2-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጕዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። ሰው ከእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤ በእነዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም። ስለዚህ ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን እንደሚቀጣህ በልብህ ዕወቅ። በመንገዶቹ በመሄድና እርሱንም በማክበር፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቅ።
ዘዳግም 8:2-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ። ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም። ሰውም ልጁን እንደሚገሥፅ እንዲሁም አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ አስተውል። በመንገዱም እንድትሄድ እርሱንም እንድትፈራ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።
ዘዳግም 8:2-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዞች ስለ መጠበቅህ በልብህ ያለውን ሐሳብ ያውቅ ዘንድ አንተን ለመፈተን በዚህ በረሓ አርባ ዓመት ሙሉ በመከራ ውስጥ በማሳለፍ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። በራብ እንድትሠቃይ አደረገህ፤ ቀጥሎም አንተም ሆንክ የቀድሞ አባቶችህ የማታውቁትን መና አበላህ፤ ይህንንም ማድረጉ ሰው ሕይወቱ ተጠብቆለት መኖር የሚችለው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አለመሆኑን ሊያስተምርህ ነው። በእነዚህም አርባ ዓመቶች ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ ከጒዞም የተነሣ እግርህ አላበጠም። አባት ልጆቹን እንደሚገሥጽ አምላክህ እግዚአብሔርም አንተን የሚገሥጽህ መሆኑን አስተውል። እርሱን በመፍራትና የእርሱንም መንገድ በመከተል፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቅ።
ዘዳግም 8:2-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ አምላክህ ሊያስጨንቅህ፥ ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ፥ በልብህ ያለውን ያውቅ ዘንድ ሊፈትንህ፥ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስታውስ። ሰው የሚኖረው በእንጀራ ብቻ ሳይሆን ከጌታ አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር ሊያሳውቅህ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን፥ አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም። እንግዲህ ሰው ልጁን እንደሚገሥፅ፥ እንዲሁም ጌታ እግዚአብሔር አንተን እንደሚገሥጽህ በልብህ አስተውል። እርሱን በመፍራትና የእርሱንም መንገድ በመከተል፥ የጌታ የአምላክህን ትእዛዞች ጠብቅ።