ዘዳግም 6:12-19
ዘዳግም 6:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ እርሱንም ተከተል በስሙም ማል። በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎች አማልክት አትከተሉ። በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳይነድድብህ፥ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ። “በፈተና ቀን እንደ ፈተንኸው አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው። ለአንተ ያዘዘውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ፥ ምስክሩንም፥ ሥርዐቱንም አጥብቀህ ጠብቅ። መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያሳድድልህ ዘንድ።
ዘዳግም 6:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከባርነት ምድር ከግብፅ ያወጣህን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዳትረሳ ተጠንቀቅ! አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ እርሱን ብቻ አገልግል፤ በስሙም ማል። በዙሪያህ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት አትከተል፤ ምክንያቱም በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ስለሆነ፣ በአንተም ላይ ቍጣው ስለሚነድድ፣ ከምድር ገጽ ያጠፋሃል። በማሳህ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አትፈታተኑት። አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጣችሁን ትእዛዞች፣ መመሪያዎችና ሥርዐቶች በጥንቃቄ ጠብቁ። መልካም እንዲሆንልህና እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶችህ በመሐላ እንድትወርሳት፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ተስፋ የሰጣቸውን መልካሚቱን ምድር ገብተህ ቀናና መልካም የሆነውን አድርግ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረትም ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ታስወጣለህ።
ዘዳግም 6:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፥ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተሉ። በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። ለእናንተ ያዘዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ምስክሩንም ሥርዓቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ። መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያወጣልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ።
ዘዳግም 6:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ባሪያ ሆነህ ትኖርባት ከነበረችው ከግብጽ ምድር ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ጥንቃቄ አድርግ። አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት አክብረው፤ እርሱን ብቻ አምልክ፤ መሐላህም በእርሱ ስም ብቻ ይሁን። በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ የሚሰግዱላቸውን ሌሎችን ባዕዳን አማልክት አታምልኩ፤ ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ በመካከላችሁ የሚገኘውን የአምላካችሁን ቊጣ ታስነሣላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ያጠፋችኋል፤ “ ‘ማሳህ’ ተብሎ በሚጠራው ቦታ እንዳደረጋችሁት ዐይነት እግዚአብሔር አምላካችሁን አትፈታተኑ፤ እርሱ ያዘዛችሁንም ትእዛዞች፥ ድንጋጌዎችና ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ። በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክልና መልካም የሆነውን ሁሉ አድርግ፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንልሃል፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ በገባውም ተስፋ ቃል መሠረት መልካሚቱን ምድር ትወርሳለህ፤ ይህንንም የምታደርገው ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ጠላቶችህን ሁሉ በማባረር ነው።
ዘዳግም 6:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን ጌታ እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። ጌታ እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፥ በስሙም ማል። በዙሪያህ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተል። በመካከልህ ያለው ጌታ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና፥ የአምላክህ የጌታ ቁጣው እንዳይነድብህ፥ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ። “ ‘በማሳህ’ እንደ ፈተናችሁት ጌታ አምላካችሁን አትፈታተኑት። ለእናንተ ያዘዘውን የጌታ የአምላካችሁን ምስክሩን፥ ሥርዓቱንም፥ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ያዙ። መልካም እንዲሆንልህ፥ ጌታም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርሷን እንድትወርስ በጌታ ፊት ትክክልና መልካሙን አድርግ። ይህም፥ ጌታ እንደሰጠህ ተስፋ፥ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ በማሳድድ ነው።