ዘዳግም 5:6-22
ዘዳግም 5:6-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። “በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር ማንኛውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ። “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በሐሰት አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በሐሰት የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። “ዕለተ ሰንበትን ጠብቅ፤ እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህም ቀድሳት። ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ በሬህም፥ አህያህም፥ ከብትህም ሁሉ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ መጻተኛ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ። አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ዕለተ ሰንበትን ትጠብቃትና ትቀድሳት ዘንድ አዘዘህ። እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ። “አታመንዝር። “ነፍስ አትግደል። “አትስረቅ። “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፤ ምስክርንም አታሳብል። “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት፥ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። “እግዚአብሔር በተራራው ላይ፤ በእሳትና በጨለማ፥ በጭጋግና በዓውሎ ነፋስ መካከል ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤያችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤ ለእኔም ሰጣቸው።
ዘዳግም 5:6-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር ላይ ባለው ወይም ከምድር በታች ውሃ ውስጥ በሚኖር በማንኛውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ)፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ለእነርሱ አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸው። ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ቸርነትንና ፍቅርን እገልጣለሁ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን ሳይቀጣው አይቀርምና፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም በከንቱ አታንሣ። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቀድሰህ አክብረው። ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሰንበት ነው። በዚህም ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማናቸውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው። በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።” እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዞቹ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዞቹንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።
ዘዳግም 5:6-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኛና አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም። የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ። አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ። እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚእብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳትና በደመናው በጨለማውም ውስጥ ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤአችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጣቸው።
ዘዳግም 5:6-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
‘በባርነት ተገዢ ሆነህ ከኖርክበት ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ “ ‘ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ። “ ‘በሰማይ፥ ወይም በምድር፥ ወይም ከምድር በታች በውሃ ውስጥ ከሚገኙት ነገሮች የተቀረጹ ምስሎች ሠርተህ አታምልካቸው፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፥ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን የሚያመልኩትን ሰዎች፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ የምበቀል ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆንኩ እነዚያን የተቀረጹ ምስሎች አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም። ለሚወዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ። “ ‘የእኔን የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሰው እግዚአብሔር ሳይቀጣው አይቀርም። “ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዝኩህ የሰንበትን ቀን ጠብቅ፤ ቀድሰውም፤ ሥራህን ሁሉ በስድስት ቀኖች ሠርተህ ታከናውናለህ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ምንም ዐይነት ሥራ አትሥራ፤ አንተም ሆንክ ልጆችህ፥ አገልጋዮችህም ሆኑ እንስሶችህ በአገርህ ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችም ቢሆኑ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ አገልጋዮችህም ልክ እንደ አንተው ዕረፍት ያድርጉ። በግብጽ ምድር ባሪያ የነበርክ መሆንህን አስታውስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይልና በብርቱ ሥልጣን ከዚያ አወጣህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብር ዘንድ ያዘዘህ ስለዚህ ነው። “ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ባዘዝኩህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል። “ ‘አትግደል፤ “ ‘አታመንዝር፤ “ ‘አትስረቅ፤ “ ‘በማንም ሰው ላይ በሐሰት አትመስክር፤ “ ‘የሌላውን ሰው ሚስቱን፥ ቤቱን፥ ርስቱን፥ አገልጋዮቹን፥ ከብቱን፥ አህዮቹንም ሆነ ማናቸውንም ንብረቱን ሁሉ አትመኝ።’ “በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር በተራራው ላይ ሆኖ ለእናንተ ለሁላችሁም የሰጣችሁ ትእዛዞች እነዚህ ናቸው፤ በእሳት፥ በደመናና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ብርቱ በሆነ ታላቅ ድምፅ በተናገረ ጊዜ የሰጣችሁ ትእዛዞች እነዚህ ብቻ ናቸው። እነርሱንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ለእኔ ሰጠኝ።
ዘዳግም 5:6-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ ‘ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ። “ ‘ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። “ ‘በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፥ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነኝና አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም። ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን አደርጋለሁ። “ ‘የጌታን የአምላክህ ስም በከንቱ አትጥራ፥ ጌታ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሳይቀጣው አይቀርምና። “ ‘ጌታ አምላክህ እንዳዘዘህ፥ እንድትቀድሰው፥ የሰንበትን ቀን ጠብቅ። ስድስት ቀን ሥራ፥ ሥራህንም ሁሉ አከናውን፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ አምላካችሁ ሰንበት ነው፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም አገልጋይህም፥ አገልጋይትህም፥ በሬህም፥ አህያህም፥ ከብትህም ሁሉ፥ ወይም በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ፥ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፥ አንተ እንደምታርፍ ሁሉ አገልጋይህና አገልጋይትህ እንዲያርፉ። አንተም በግብጽ ባርያ እንደ ነበርህ አስታውስ፥ ጌታ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ። “ ‘ጌታ አምላክህ እንዳዘዘህ፥ ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ፥ አባትህንና እናትህን አክብር። “ ‘አትግደል። “ ‘አታመንዝር። “ ‘አትስረቅ። “ ‘በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “ ‘የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፥ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም አገልጋዩንና አገልጋይቱን፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ንብረት ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።’ “እነዚህን ቃሎች ጌታ በተራራው ላይ ለጉባኤአችሁ ሁሉ በእሳትና በደመና፥ በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ ሆኖ፥ በታላቅ ድምፅ ተናገረ፥ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጠኝ።