ዘዳግም 4:32-40

ዘዳግም 4:32-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰውን በም​ድር ላይ ከፈ​ጠ​ረው ጀምሮ፥ ከሰ​ማይ ዳር እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ከቶ እን​ዲህ ያለ ታላቅ ነገር ሆኖ፥ ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰ​ምቶ እንደ ሆነ ከአ​ንተ በፊት የነ​በ​ረ​ውን የቀ​ደ​መ​ውን ዘመን ጠይቅ። አንተ ከእ​ሳት መካ​ከል ሆኖ ሲና​ገር የሕ​ያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ድምፅ እንደ ሰማ​ህና በሕ​ይ​ወት እን​ዳ​ለህ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ እንደ ሆነ፥ አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዐ​ይ​ና​ችሁ ፊት በግ​ብፅ ለእ​ና​ንተ እንደ ሠራው ሁሉ ፥ በፈ​ተ​ናና በተ​አ​ም​ራት፥ በድ​ን​ቅና በሰ​ልፍ፥ በጸ​ናች እጅና በተ​ዘ​ረጋ ክንድ፥ በታ​ላ​ቅም ማስ​ፈ​ራ​ራት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከሌላ ሕዝብ መካ​ከል ገብቶ ለእ​ርሱ ሕዝ​ብን ይወ​ስድ ዘንድ ሞክሮ እንደ ሆነ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አም​ላክ እንደ ሆነና ከእ​ር​ሱም ሌላ አም​ላክ እንደ ሌለ እን​ድ​ታ​ውቅ፥ ያስ​ተ​ም​ርህ ዘንድ ከሰ​ማይ ድም​ፁን አሰ​ማህ፤ በም​ድ​ርም ላይ ታላ​ቁን እሳት አሳ​የህ፤ ከእ​ሳ​ቱም መካ​ከል ቃሉን ሰማህ። አባ​ቶ​ች​ህን ወድ​ዶ​አ​ልና ከእ​ነ​ርሱ በኋላ ዘራ​ቸ​ውን መረጠ፤ ከአ​ን​ተም ጋር ሆኖ በታ​ላቅ ኀይሉ ከግ​ብፅ አወ​ጣህ፤ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከግ​ብፅ ከአ​ንተ የጸ​ኑ​ትን ታላ​ላ​ቆ​ቹን አሕ​ዛብ በፊ​ትህ እን​ዲ​ያ​ወጣ፥ አን​ተ​ንም እን​ዲ​ያ​ገ​ባህ፥ ምድ​ራ​ቸ​ው​ንም ርስት አድ​ርጎ እን​ዲ​ሰ​ጥህ፥ እን​ግ​ዲህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በላይ በሰ​ማይ በታ​ችም በም​ድር አም​ላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደ ሌለ ዛሬ ዕወቅ፤ በል​ብ​ህም ያዝ። ለእ​ና​ንተ፥ ከእ​ና​ን​ተም በኋላ ለል​ጆ​ቻ​ችሁ መል​ካም ይሆን ዘንድ፥ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለዘ​ለ​ዓ​ለም በሚ​ሰ​ጣ​ችሁ ምድር ዕድ​ሜ​አ​ችሁ ይረ​ዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማ​ዝ​ዛ​ች​ሁን ሥር​ዐ​ቱ​ንና ትእ​ዛ​ዙን ጠብቁ።”

ዘዳግም 4:32-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን ጀምሮ እናንተ ከመኖራችሁ በፊት ስለ ነበረው የቀድሞ ዘመን ጠይቁ፤ ከአንዱ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው የሰማይ ጫፍ ድረስ ጠይቁ፤ እንደዚህ ያለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ወይስ እንደዚህ ዐይነት ነገር ከቶ ተሰምቶ ያውቃልን? ከእሳት ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ እናንተ የሰማና በሕይወት የኖረ ከቶ ሌላ ሕዝብ አለን? አምላካችሁ እግዚአብሔር በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብጽ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን? እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን፣ ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ። ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋራ በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብጽ አወጣህ፤ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ከፊትህ በማስወጣት ወደ ምድራቸው አስገብቶህ ለአንተ ርስት አድርጎ ለመስጠት ነው። እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም። ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህም ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ጠብቅ።

ዘዳግም 4:32-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቃ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን? አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን? እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ፤ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ፤ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።

ዘዳግም 4:32-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እናንተ ከመወለዳችሁ በፊት በነበረው ዘመን ያለፈውን ነገር ሁሉ እስቲ መርምሩ፤ ምድርን በሞላ መርምሩ፤ ከዚህ በፊት ይህን የመሰለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ያውቃልን? እንደዚህ ያለውን ነገር የሰማ ከቶ አለ ይሆን? እናንተ በሰማችሁት ዐይነት እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ውስጥ ሆኖ ተናግሮት በሕይወት ለመኖር የቻለ ሕዝብ ከቶ አለን? ወይስ በፈተና፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራ ኀይል፥ በዐይናችሁ እያያችሁት እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ያለ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? አምላክ እርሱ ብቻ እንደ ሆነና ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጥላችሁ ዘንድ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አሳይቶአችኋል፤ እናንተን ለማስተማር ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፤ በምድርም አስፈሪ እሳቱን እንድታዩ ፈቀደላችሁ፤ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ። የቀድሞ አባቶቻችሁን በመውደዱ እናንተን ልጆቻቸውን ስለ መረጣችሁ በታላቅ ኀይሉ እርሱ ራሱ ከግብጽ አወጣችሁ። ይህንንም ማድረጉ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ከእናንተ የሚበልጡትንና ኀያላን የሆኑትን ሕዝቦች አስወጥቶ ምድራቸውን ለእናንተ ርስት ለማድረግ ነው። ስለዚህም በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱ ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤ በልባችሁም ያዙት። እግዚአብሔር አምላካችሁ ለዘለዓለም እንድትኖሩባት በሚያወርሳችሁ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖሩ ዘንድ ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም እንዲሆንላቸው እኔ ዛሬ የማዛችሁን ሕጉንና ትእዛዞቹን ጠብቁ።”

ዘዳግም 4:32-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጊዜ ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። እናንተን ከእሳት ውስጥ ሆኖ እንደ ተናገረው፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት መኖር የቻለ፥ ሌላ ሕዝብ ከቶ አለን? ወይስ በፈተና፥ በተአምራት፥ በድንቅ፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራም ኃይል፥ በዐይናችሁ ፊት ጌታ አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ፥ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? ጌታም አምላካችሁ እንደሆነ እንድታውቁ ይህ ለእናንተ ተገልጧል፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። ያስተምራችሁ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፥ በምድርም ላይ ታላቁን እሳቱን አሳያችሁ፥ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ።። አባቶቻችሁን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ከእናንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብጽ አወጣችሁ። ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ፥ ከእናንተ የበረቱትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊታችሁ እንዲያስወጣ፥ እናንተንም እንዲያስገባ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው። እንግዲህ፥ ጌታ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቁ፥ በልባችሁም ያዙት። ለእናንተ፥ ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም ይሆን ዘንድ፥ ጌታ አምላካችሁ ለዘለዓለም በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዛችሁን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቁ።”