ዘዳግም 17:8-11
ዘዳግም 17:8-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“በደምና በደም መካከል፥ በፍርድና በፍርድ መካከል፥ በመቍሰልና በመቍሰል መካከል፥ በክርክርና በክርክር መካከል በሀገርህ ውስጥ ሰዎች ስለሚከራከሩበት ክርክር የሚሳንህ የፍርድ ነገር ቢኖር፥ አንተ ተነሥተህ ስሙ በዚያ ይጠራ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትወጣለህ፤ ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ አሉ ፈራጆች መጥተህ ትጠይቃለህ፤ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። ስሙ በዚያ ይጠራ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ እንደ ነገሩህ ቃል ታደርጋለህ፤ ያስተማሩህንም ሕጉን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። እንዳስተማሩህም ሕግ፥ እንደ ነገሩህም ፍርድ አድርግ፤ ከነገሩህ ፍርድ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
ዘዳግም 17:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንድ የነፍስ ግድያ ዐይነትና በሌላ፣ በአንድ ዐይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፣ ወይም በአንድ የክስ ዐይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጕዳይ ቢነሣ፣ ከዐቅምህ በላይ የሆነ ጕዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፣ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ፤ ካህናት ወደ ሆኑት ሌዋውያንና በዚያን ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄደህ ስለ ጕዳዩ ጠይቃቸው፤ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል። አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም። እንድትፈጽም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ። በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። እነርሱ ከሚነግሩህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
ዘዳግም 17:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በደምና በደም፥ በፍርድና በፍርድ፥ በመቁሰልና በመቁሰል መካከል በአገርህ ደጅ ውስጥ ሰዎች ስለሚከራከሩበት ክርክር የሚሳንህ የፍርድ ነገር ቢነሣ፥ አንተ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትወጣለህ፤ ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ ተሾመው ፈራጅ መጥተህ ትጠይቃለህ፤ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ የነገሩህን የፍርድ ነገር ታደርጋለህ፤ እንዳስተማሩህም ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። እንዳስተማሩህም ሕግ፥ እንደ ነገሩህም ፍርድ አድርግ፤ ከነገሩህ ፍርድ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
ዘዳግም 17:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“በደም ማፍሰስ፥ በሰብአዊ መብት፥ በግድያ ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች በከተሞችህ በሚነሡ ክርክሮች የፍርድ አሰጣጡ አስቸጋሪ ቢሆንብህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ፈጥነህ በመሄድ ከሌዋውያን ወገን ካህናት ለሆኑትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ለሆነው ጉዳዩን አቅርብ፤ ጉዳዩንም እነርሱ ይወስኑ። እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ ሆነው የሚሰጡህን ውሳኔ በትክክል እሥራ ላይ አውል፤ እነርሱም የሚነግሩህን በጥንቃቄ ጠብቅ። በሚሰጡአችሁ መመሪያና ሕግ መሠረት ሁሉን አድርጉ፤ ከዚያም ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ፈቀቅ አትበሉ።
ዘዳግም 17:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በአንድ የነፍስ ግድያ ዓይነትና በሌላ፥ በአንድ ዓይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፥ ወይም በአንድ የክስ ዓይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጉዳይ ቢነሣ፥ ከአቅምህ በላይ የሆነ ጉዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፥ ተነሥተህ አምላክህ ጌታ ወደ መረጠው ስፍራ ውጣ፤ ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ ተሾመው ፈራጅ መጥተህ ትጠይቃለህ፥ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። አንተም ጌታ በመረጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም፤ ለመፈጸም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ። በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። ከሚነግሩህ ቀኝም ግራም አትበል።